Logo
YenetaTube
ዚምባብዌ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚወሰድ አዲስ የኤች አይቪ መከላከያ መድኃኒት በይፋ አስጀመረች

ዚምባብዌ በዓመት ሁለት ጊዜ በመርፌ የሚሰጥና ውጤታማነቱ አስተማማኝ የሆነውን "ሌናካፓቪር" (Lenacapavir) የተሰኘ የኤች አይቪ መከላከያ መድኃኒት በብሔራዊ ደረጃ በይፋ በማስጀመር ከአለም ቀዳሚዋ ሀገር ሆናለች።

የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዳግላስ ሞምቤሾራ (ዶ/ር) መድኃኒቱ ኤድስን እንደ የህዝብ ጤና ስጋት ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በጊልያድ ሳይንስ (Gilead Sciences) የበለጸገውና ባለፈው ህዳር ወር በሀገሪቱ የፈቃድ ማረጋገጫ ያገኘው ይህ መድኃኒት፣ በየቀኑ የሚወሰዱ የቅድመ ተጋላጭነት መከላከያ (PrEP) መድኃኒቶችን አስፈላጊነት የሚያስቀር ነው።

በመጀመሪያው ምዕራፍ በ24 ማዕከላት ውስጥ ለሚገኙ 46 ሽህ ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች ይሰጣል የተባለ ሲሆን፤ ቅድሚያ ለወጣት ሴቶች፣ ለታዳጊዎች እና ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሰጥም ይሆናል፡፡

ፕሮጀክቱ በአሜሪካ መንግስት እና በግሎባል ፈንድ ድጋፍ የሚከናወን ነው። መድኃኒቱ በዓመት ሁለት ጊዜ በመርፌ የሚሰጥ ሲሆን፤ ከሞላ ጎደል መቶ በመቶ የመከላከል አቅም እንዳለው ተረጋግጧል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) በበኩላቸው ይህንን አዲስ መድኃኒት "ከክትባት ቀጥሎ ያለ ምርጥ አማራጭ" ሲሉ ማወደሳቸውን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡

በዚምባብዌ በአሁኑ ወቅት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከኤች አይቪ ጋር የሚኖሩ ቢሆንም፣ ሀገሪቱ የተያዘውን የሶስቱን 95 የህክምና ግቦች ማሳካት የቻለችና የበሽታውን ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰች ሀገር መሆኗ ይነገራል።

@የኢትዮጵያ_ፕሬስ_ድርጅት

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.