Logo
FastMereja
ጥቂት ትዝብቶች . . .የሚኒስትሩ

ንግግር ምንም አስተያየት አያሻውም። ጥሬ ሐቅ ነው። የጋጠወጥ ሹፌሮች ከተማ ነች ዋና ከተማችን። እኔ ራሴ ከሞላ ጎደል ትሁት (Semi-humble 🌚) ነኝ ብዬ አምናለሁ። ከመሪ ጀርባ ስሆን ግን አይደለሁም፤ በብዙ ምክንያት!

"ይቅርታ!" የሚል ቃል የሚወጣው ሹፌር ማየት የፀሀይ ግርዶሽ የማየት ያህል ብርቅ ነው!

እግረኛ ላሳልፍ ብሎ የቆመ ሹፌር ከኋላው ከሚመጡት ስድብ ይሸለማል፣ በክላክስ ጆሮው ይደማል። የተከለከለ ቦታ ማቆም፣ እግረኛ ውሀ ረጭቶ ማለፍ፣ ወዘተ የተለመዱ ናቸው። ዜብራ መሻገሪያ ላይ ለእግረኛ ቅድሚያ ያለመስጠት ብቻ በአግባቡ ቅጣት ቢጣልበት መንግስት በዓመት አንድ ሁለት ቢልየን ብር ሐቁ ነበር።

Road rage እየተባባሰ መጥቷል። "እንዴት አላስቀደምከኝም?" ብሎ (ቅድሚያ መብት ሳይኖረው) ከፊት አልፎ መንገድ ዘግቶ፣ ከመኪና ወርዶ ካልደበደብኩ የሚል ጥጋበኛ ፈልቷል። ብቻ አሽከርካሪዎች በጥፋታቸው ልክ አይቀጡም የሚለው ያስማማኛል።

ነገር ግን በአንፃሩ ሊታረሙ የሚገቡ እጅግ ብዙ ጥፋቶች በመንግሥት በኩል አሉ። የትራፊክ ሕግ የመጣስ ስልጠናን በተግባር ለሕዝቡ የሚሰጡት የመንግሥት መኪኖችን፣ ቪአይፒ ባለሀብቶች መኪኖችን እና የተለያዩ መያዶች (AU, UN, AO, & CD plates) አንድ ካልተባሉ ቅጣትና ሕግ ማስከበሩ አድሏዊ ይሆናል። አፍላ ወጣት የባለሥልጣን ልጆች የመኪና እሽቅድድም ሲያደርጉ ነው የሚል የከተማ ራሊ መሳይ ቪዲዮ በቅርቡ አይተናል። ይሄ ደግሞ ነውር ነው።

መንገዶች አመቺ ያልሆኑባቸው ቦታዎች ላይ መንገድ መረጣ ለትራፊክ አደጋ ያጋልጣል። በሌላ በኩል ደግሞ ሰፋፊ፣ ሰው የማይበዛባቸው፣ የአደጋ ታሪክ የሌላቸው እና በቂ ጥናት ያልተደረገባቸው ቦታዎች ላይ የፍጥነት ወሰን 50 ኪሜ/ሰዓት ይሆናል። በቀላሉ ማለፍ የሚችለው ተሽከርካሪ ይደራረባል። ሹፌር ከመንገዱ ላይ ዓይኑን ነቅሎ አስር ጊዜ የፍጥነት ጌጁን ያያል። የነዳጅ መስጫ ፔዳሉን የሚጫነው የሰው እግር ነው። ፕሮግራም የተደረገ ማሽን አይደለም። ትንሿ የእግር እንቅስቃሴ ከ50 ወደ 60 ኪሜ/ሰዓት ሳታስበው ነው የሚያደርስህ። ቅጣት ፈርተህ ዓይንህን ከመንገድ ስትነቅልም ሆነ ቅጣት ፈርተህ ፍሬን ስትይዝ አደጋ ትፈጥራለህ።

የፍጥነት ወሰንን መጣስ ማስቀጣት ያለበት ለኖቶሪየስ ጥሰት ነው። መጠነኛ መዋዠቅ በይቅርታ ነው መታለፍ ያለበት። ይሄ ይቅር የሚባል የመዋዠቅ ህዳግ (margin) ከ5 ኪሎሜትር ከፍ ማለት አለበት። የሹፌሩ ሀሳብ ሕግ ጥሶ መሄድ ወይም ድንገተኛ የፍጥነት መዋዠቅ መሆኑን ከአነዳዱ መለየት ይቻላል። በጠራራ ፀሀይ በ50 መንገድ ላይ ከ8ዐ ክስከ 100 የሚነዳ አለ። እሱን ከሆነች ራዳር ዕይታ ውስጥ ከገባች ቅፅበታዊ የ60 ኪ/ሜ ፍጥነት ጋር እኩል መቅጣት ፍትሐዊ አይሆንም።

ከዚህ በተጨማሪ ያለጥፋት የሚቀጡ የተወሰኑ ትራፊኮችና የትራፊክ አስተባባሪዎች ሀይ ሊባሉ ይገባል። አጠፋህ ለሚሉት ጥፋት ማስረጃ የላቸውም፣ አንዳንዴ ከጀርባው ቆመው ባላዩት መብራት ሁሉ ይቀጣሉ። ቅጣቱን አሜን ብለህ የመቀበል ግዴታ ግን አለብህ። አንዳንዴ የፍጥነት ገደብ ጣስክ ስትባልም ያው ነው። አሳዩኝ ስትል ራዳሩን የያዘው ባለሙያ ለምሳ እስኪመጣ ጠብቅ ትባላለህ። ለሰዓታት ከመቆም ተቀጥቶ መሄድን ያስመርጡሀል። በነገሮች ተከልሎ በፍጥነት መለኪያ ራዳር ለማጥመድ መሞከርም ተገቢ አይደለም። የትራፊክ ፖሊሶችና አስተናባሪዎች ለሕዝቡ መታየት አለባቸው። አሽከርካሪ አይቷቸውና እነሱ አሉ ብሎ ሕግ ማክበሩ ነው በጊዜ ሒደት የሕግ ማክበርን ባሕል የሚያደርገው። ተደብቆ ሕግ እስኪጥሱ መጠበቅ ማለማመድ ነው።

አሽከርካሪን እንደ ሌባ አይተው አክብሮት በሌለው መንገድ የሚያናግሩበት መንገድ ከሁሉም አናዳጁ ነው። ለአንዳንድ ባለሀብት እና ቲንትድ መኪና ባለቤቶች በወታደራዊ ሰላምታ ጭምር እጅ ሲነሱ ባየንበት ዓይን፣ የነሱና የልጆቻቸው ሀኪም፣ መምህር ወዘተ ሊሆን የሚችልን ሰው ሲያበሻቅጡና ሲያመናጭቁ ማየት የምር ያሳዝናል።

ለአንድ አንቀፅ የጀመርኩት ፅሑፍ ነው። ለካ ብዙ ነው ብሶታችን። ይብቃኝ።

በገመቹ መራራ

6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.