Logo
FIDEL POST NEWS
የሱዳን ቀውስ፡ በወርቅ እያበራ፣ በረሃብ እያለቀሰ

​ሱዳን በዘር ማጽዳት፣ አስገድዶ መድፈር፣ 4.3 ሚሊዮን የሚሆኑ የተፈናቀሉ ሰዎች እና በከባድ የምግብ ቀውስ የተመታች የአፍሪካ ሀገር ነች።

በሱዳን ባለው የዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ቢያንስ 150,000 ሰዎች ተገድለዋል። በዚህ ሁኔታ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሱዳንን በዓለም ላይ እጅግ የከፋ ሰብአዊ ቀውስ ያለባት ሀገር አድርጎ አውጇል።

በዚህች ሀገር ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ማዕድናት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቶን ወርቅ አለ።

በተጨማሪም፣ በነዳጅ በበለፀገችው ሱዳን ውስጥ በእነዚህ በጥቁር ገበያ በተሸጡት ሀብቶች የተገኘው ገንዘብ በርስ በእርስ ጦርነቱ ውስጥ ሚና እየተጫወተ ነው። ወርቁ ቢኖርም በአስተዳደር መጓደል እና በስልጣን ሽኩቻ ምክንያት በሀገሪቱ ውስጥ ቢያንስ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች በረሃብ እየተሰቃዩ ነው።

​የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ታሪክ

​ሱዳንከፈረንጆቹ እስከ 1956 ድረስ በእንግሊዝ እና በግብፅ ትተዳደር ነበር። በግብፅ እርዳታ ሀገሪቱ ጥር 1956 ነፃነቷን አገኘች። ከዚያ በኋላ በደቡብ ሱዳን እና በአሁንዋ ሱዳን መካከል የዘር እና የሃይማኖት ግጭት የነበረ ሲሆን ረጅም ግጭት ተፈጠረ። በ1983 ፕሬዝዳንት ጃዓፋር ኑማን የእስልምናን ሸሪዓ ህግ ሲያስተዋውቁ ከደቡብ ሱዳን ጋር ከባድ የእርስ በእርስ ጦርነት ተጀመረ።

በዚህ ሁኔታ የሱዳን ወታደራዊ እና እስላማዊ የፖለቲካ መሪዎች ያቀዱት መፈንቅለ መንግስት ተካሄደ። ኦማር አልበሽር ሰኔ 1989 በመፈንቅለ መንግስቱ ሱዳን ውስጥ ስልጣን ያዙ። በወቅቱ አልበሽር በሱዳን ጦር ሰራዊት ደህንነት ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ያለው መኮንን ነበሩ። መፈንቅለ መንግስቱን የመሩት እሳቸው ነበሩ።

​ነገር ግን በ2019 አልበሽር አሰቃቂ እጣ ፈንታ ውጤቶችን መቀበል ነበረባቸው። በ2019 በሱዳን በእርሳቸው ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ተነሳ። በዚህም ምክንያት ጦር ሠራዊቱ በሌላ መፈንቅለ መንግስት ፕሬዝዳንቱን ገለበጠ። ሆኖም፣ ተራው ሕዝብ ዲሞክራሲ እንሰፍን በመጠየቅ ተቃውሞውን ቀጠለ። በተቃውሞው ጫና የሠራዊቱና የሲቪል አስተዳደሩ በጋራ ተነሳሽነት መንግሥት የተቋቋመ ቢሆንም፣ ያ መንግሥትም በጥቅምት 2021 በሌላ መፈንቅለ መንግስት ተወገደ።

​ከመፈንቅለ መንግስቱ ጀርባ የነበሩት ሁለቱ ዋና ዋና ሰዎች ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና ጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ናቸው። ጄኔራል አል-ቡርሃን የሱዳን የታጠቁ ኃይሎች (ሠራዊቱ) መሪ እና የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ናቸው። ሃምዳን ዳጋሎ የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች (RSF) አዛዥ ናቸው። በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች መሠረት፣ ይህ መጥፎ ስም ያተረፈው ከፊል ወታደራዊ ኃይል (RSF) በሱዳን ውስጥ የተለያዩ ሰብአዊ ወንጀሎችን እየፈፀመ ነው። የቡርሃን እና የዳጋሎ ኃይሎች ለሱዳን ቀውስ ተጠያቂ ናቸው።

​የጦርነቱ ዋና አቅርቦቶች ወርቅ እና ነዳጅ ናቸው

​በሱዳን ውስጥ በተገኙ የተለያዩ ማዕድናት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቶን ወርቅ ተከማችቷል ተብሎ ይነገራል። በተጨማሪም፣ ተጨማሪ ማዕድናት ሳይገኙ አሉ ። በሱዳን ውስጥ ትልቁ የወርቅ ማዕድን ቦታ ጀበል አመር ነው። ማዕድኑ በቀጥታ በRSF ቁጥጥር ስር ነው። ከዳጋሎ ቤተሰብ ጋር የተቆራኘው አል-ጁናይድ ኩባንያ ማዕድኑን ሲያስተዳድር ቆይቷል። በተጨማሪም በዳርፉር እና በደቡብ ኮርዶፋን ክልሎች ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ የወርቅ ማዕድናት በአሁኑ ጊዜ በRSF ቁጥጥር ስር ናቸው።

​በ2024 RSF ከእነዚህ ማዕድናት ቢያንስ 10 ቶን ወርቅ አውጥቷል፣ የገበያ ዋጋውም 860 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው። ሁለቱ ትልልቅ ገዢዎች የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ግብፅ ናቸው። ከዚህ ወርቅ ውስጥ 80 በመቶው በህገ-ወጥ መንገድ ይዘዋወራል። ለህገ-ወጥ ዝውውር በጣም የታወቀው መንገድ ከዳርፉር ድንበር ክልል ወደ ግብፅ በኢትዮጵያ በኩል ነው።

ሌላው ከዳርፉር ድንበር ክልል ወደ ሊቢያ ከዚያም ወደ ኤሚሬትስ ነው። በተጨማሪም RSF በታኅሣሥ መጀመሪያ የሱዳንን ትልቁ የነዳጅ መስክ የሆነውን ሄግሊግን ተቆጣጥሯል። ዜጎችን ለመግደል እየዋለ ያለው መሳሪያ በወርቅና በነዳጅ ገንዘብ እየተገዛ ነው።

​አስከፊ ሰብአዊ ቀውስ እና የዋጋ ግሽበት

​ግጭቱ በመላው ሱዳን ከ150,000 በላይ ሰዎችን ገድሏል። ረሃብ በሀገሪቱ ተስፋፍቷል። ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ቤታቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶችም ተደፍረዋል።
​ዓለም አቀፉ የስደት ድርጅት (IOM) እንደገለጸው በሱዳን ውስጥ 30 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ 9.6 ሚሊዮን የሚሆኑት በውስጥ ተፈናቃዮች ሲሆኑ፣ 4.3 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ወደ ጎረቤት አገሮች ተሰደዋል።

በተጨማሪም ከ700,000 በላይ ሕጻናት በከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ሲሆን ከ2.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል።
​ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የሱዳን ፓውንድ ያለማቋረጥ ዋጋው እየቀነሰ ነው። በ2025 በሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት 113 በመቶ ደርሷል።

​የዩኒሴፍ ባለስልጣን ቴድ ቻይባን እንደተናገሩት በችግሩ በከፋ ሁኔታ የተጎዱት ህጻናት ናቸው። ወደ 1.4 ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት በረሃብ ስጋት ውስጥ ሲሆኑ፣ 14 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው፣ ይህም በሱዳን ውስጥ ካሉት ህጻናት አራት አምስተኛው ነው። በሰሜን ዳርፉር ብቻ በዚህ ዓመት 150,000 ሕጻናት በከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው።

​ምንጭ፡ ሚድል ኢስት ሞኒተር/ቢቢሲ/አልጀዚራ
8 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.