Logo
YenetaTube
6ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር “የሳይበር ደህንነት - የዲጂታል ኢትዮጵያ መሰረት” በሚል መሪ ቃል ይከበራል

አዲስ አበባ፡ መስከረም 29/2018 ዓ.ም፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ከጥቅምት 1-30/2018 ዓ.ም ድረስ የሚከበረውን 6ኛውን ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ፡፡

ዋና ዳይሬክተሯ በመግለጫቸው 6ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር “የሳይበር ደህንነት - የዲጂታል ኢትዮጵያ መሰረት” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮች እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡

በሀገራችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ከማደጉ ጋር ተያይዞ በዜጎች፣ በተቋማት እና ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመው፣ የሳይበር ደህንነት ወር የተቋማትን እና የኅብረተሰቡን የሳይበር ደህንነት ንቃተ-ህሊና በማጎልበት ለሳይበር ደህንነት ተገቢ ትኩረት እንዲሰጡና እራሳቸውን ከሳይበር ጥቃት መከላከል እንዲችሉ የሚያግዙ የተለያዩ መርሐግብሮች የሚካሄዱበት ወር እንደሆነ ገልጸዋል።

6ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር በሁለት ዋና ዋና ጭብጦች እንደሚከበር የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፤ የመጀመሪያው የሃሰተኛ መረጃ ዝግጅትና ስርጭት መከላከል ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ዲጂታላይዜሽን እና የሳይበር ደህንነት ጋር የሚያተኩር ነው፡፡

6ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር የመክፈቻ መርሃ ግብር ጥቅምት 1/2018 ዓ/ም በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና መ/ቤት የሚከፈት ሲሆን፤ በእለቱ “የሃሰተኛ መረጃ ዝግጅት፣ ቁጥጥርና ስርጭት (Disinformation and misinformation in the AI era)” በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ ይካሄዳል፡፡ በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ጋር ተያይዞ የተሰራ ጥናት እንደሚቀርብም ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ገልጸዋል፡፡ ከውይይቱ ባሻገር በእለቱ ታዳጊዎችንና ወጣቶችን የሚያሳትፍ Catch the Flag – CTF ውድድር ይካሄዳል፡፡

በሁለተኛ እና ሦስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር “ዲጂታላይዜሽን እና የሳይበር ደህንነት ላይ ትኩረት በማድረግ በሁለት የክልል ከተሞች የውይይት መድረክ የሚካሄድ ይሆናል፡፡

ከላይ ከሚካሄዱት መርሃ ግብሮች ባሻገር የጥቅምት ወርን ሙሉ ቀናት የሕብረተሰቡንና የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊና የሚያጎለብቱ የሚዲያ ንቅናቄ ሥራዎች እንደሚሰሩ ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ተናግረዋል፡፡ በሌላም በኩል በዩኒቨርሲቲዎችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይበር ደህንነት ክበባትን ለማበረታታት የሚያስችሉ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ በተጨማሪም ዜጎችን የሚያሳትፉ የሳይበር ደህንነት ንቃተ-ህሊናን የሚያጎለብቱ የተለያዩ ውድድሮች ይካሄዳሉ፡፡ በዚህም ዜጎች ስለሳይበር ደኅንነት ያላቸውን ግንዛቤ የሚገመግሙበትና የተለያዩ ሽልማቶችን የሚያገኙበት ይሆናል:: ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ ሽልማት የሚያስገኙ የማህበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ እና የአጭር ፊልም ውድድሮች መዘጋጀታቸውን ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡

ኢመደአ የሀገሪቱን የሳይበር ደህንነት የማስጠበቅ የመሪነት ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በተመሳሳይ የመንግስትና የግል ተቋማት የሳይበር ደህንነትን የማረጋገጥ ሥራ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን በመረዳት የጥቅምት ወርን የሰራተኞቻቸውን የሳይበር ደህንነት ንቃተ-ህሊና ለማሳደግ የሚያስችሉ የንቅናቄ ሥራዎችን በመከወን እንዲያከብሩ ዋና ዳይሬክተሯ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ እንዲሁም የሚዲያ አካላት በዚህ ወር የኅብረተሰቡን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ የሚያጎለብቱ ይዘቶችን ትኩረት በመስጠት በስፋት እንዲያስተላልፉ ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሳይበር ደህንነት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ ለ22ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን በኢትዮጵያ ለ6ኛ ጊዜ የሚከበር ይሆናል፡፡

ተጨማሪ የሳይበር ደህንነት መረጃዎችን ለማግኘት፡-
• ድረ ገጽ፦ https://www.insa.gov.et
• ቲክቶክ፡- https://www.tiktok.com/@in...
• ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/@c...
• ቴሌግራም፦ https://t.me/insagovet
• ትዊተር (X) ፦ https://twitter.com/INSAEt...
• የሳይበር ጥቃት ጥቆማ ለመስጠት ነጻ የስልክ መስመር፡ 933

10 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.