Logo
YenetaTube
ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዘመናት አንቀላፉ

በከሀዲው ንጉሥ ዳኬዎስ ዘመን በኤፌሶን የነበሩ ቅዱሳን ሲሆኑ ሰባቱ ደቂቅ ተብለው የሚጠሩ ዳኬዎስ ከጭፍሮቹ መርጦ በመዛግብቱ ላይ የሾማቸው ነበሩ። ንጉሡ አምልኮ ጣዖትንም በአወጀ ጊዜ ጣዖትን በማምለክ ሥራ አልተሳተፉም። ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ አሠራቸው። ወደ ሌላ ቦታ ሊሔድ ሲልም ምናልባት ከምክራቸው ቢመለሱ ብሎ አስቦ እስከሚመለስ ድረስ ፈትቶ ለቀቃቸው። ከዚህም በኋላ እሊህ ቅዱሳን ለረከሱ ጣዖታት እንዳይሰግዱ የጭፍራነት ሥራቸውን ትተው በተራራ ውስጥ ወዳለ ዋሻ ሒደው የዋሻውን አፍ ዘግተው ተሠወሩ፡፡ በየተራም እየወጡ ምግባቸውን ገዝተው ይመለሱ ነበር። ዳኬዎስም ከሔደበት እንደተመለሰ በሰሙ ጊዜ የዋሻውን ደጃፍ ዘግተው ተኙ። ከጭፍሮች አንድ አማኒ ቦታቸውን ያውቅ ነበርና ወደ ከተማ ሲወጡ ሊያገኛቸው ቢጠብቃቸውም ሲጠፉበት ተነሥቶ ወደ ዋሻቸው ሔደ።

ዋሻዋንም ከውስጥ እንደ ዘጓት ሆና ስላገገኛት በረሀብ የሞቱ መሰለው፤ የደንጊያ ሠሌዳም አምጥቶ ከእሳቸው የሆነውን ገድላቸውን ጽፎ በቀዳዳ ወደ ዋሻው ውስጥ አስገባው። እኒህም ቅዱሳን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዘመናት አንቀላፉ ዳኬዎስም ሙቶ እስከ ቴዎዶስዮስ በርካታ ነገሥታት ነገሡ። በዚህም ምእመን ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዘመን ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዎች ተነሥተው ብዙዎች ተከተሏቸው። ያን ጊዜም ትንሣኤ ሙታን መኖሩን ግልጽ ያደርግ ዘንድ እነዚህን ቅዱሳን ሰባቱን ደቂቅ እግዚአብሔር አነቃቸው። ከዚህም በኋላ ከእርሳቸው አንዱ ምግባቸውን ሊገዛ የከሀዲው ንጉስ ዳኪዎስንም ወሬ ይሰማ ዘንድ የእርሱ ምልክት ያለበትን ገንዘብ ይዞ ወጣ ወደ ከተማም ሲገባ በበሯ ላይ መስቀሎችን አየ፣ በየቅጽሮቿም የክብር ባለቤት የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስሙን ያለ መፍራት ሲጠሩ ሰማ፣ ያን ያህል ዘመን ተኝተው መንቃታቸውን አላወቁምና፡፡

አንዱንም ሰው ይች አገር ኤፌሶን አይደለችምን ብሎ ጠየቀ እርሱም አዎን ናት አለው። ያንንም ገንዘብ አውጥቶ ምግባቸውን ሊገዛ ሲል ሻጩ የንጉሥ ዳኬዎስም ስም ተቀርጾበት ተመለከተው፡፡ ቅዱሱንም በአንተ ዘንድ የተሸሸገ ሀብት አለ፣ ይህ ምልክት ከአንተ ተገኝቷልና አለው። የዚያውም አገር ተወላጅ እንደሆነ ሲነግራቸውም “ማንን ታውቃለህ?” አሉት የጠራቸው ስሞች ግን በዘመን ብዛት ተረስተዋል። ተቆጥተውም ወደ ኤጲስቆጶስ አባ ቴዎድሮስና ወደ ንጉሥ ቴዎዶስዮስም አቀረቡት። እነርሱም እውነቱን እንዲናገር ጠየቁት። እርሱም ሰባታችን የከሀዲው ንጉሥ ዳኬዎስ ጭፍሮች ነን ወደ ሌላ ሀገር ሲሔደ ከአንዷ ዋሻ ውስጥ ገብተን በሩን ዘግተን ተኛን። ስንነቃም የምንመገበውን ምግብ እንድገዛ ላኩኝ። ንጉሡና ኤጲስቆጶሱ ይዘውት ወደ ዋሻው ሔዱ፡፡ ብዙ ሕዝብም ተከተላቸው፤ ቅዱሳኑንም ተቀምጠው አገኙአቸው።

ያ ክርስቲያን የጻፈበትን ሠሌዳም ወድቆ አገኙት፤ ዘመኑም 372 ዓመት እንደሆነ ታወቀ። ንጉሡ፣ ኤጲስቆጶሱና ሕዝቡ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት፡፡ ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉትም ይህን ድንቅ ሥራ አይተው ትንሣኤ ሙታን እንዳለ አመኑ። እሊህ ሰባቱ ደቂቅንም ሲጠይቋቸው የሆነውን ሁሉ ነገሩአቸው። ተመልሰውም ተኝተው ነፍሳቸውን በእግዚአብሔር እጅ ሰጡ። ንጉሥም በወርቅ ሣጥን በሐር ልብሶችም ገንዞ በመልካም ቦታ አኖራቸው። ከሥጋቸውም ብዙ ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ። ሰባቱ ቅዱሳንም መክሲማኖስ፣ ታሙኪሮስ፣ መርዳዲሞስ፣ ዮሐንስ፣ ቈስጠንጢኖስ፣ አዝሚና ዲዮናስዮ ይባላሉ። ገዳማውያን የቅዱሳንን በረከት እያሰቡ በጸሎት ይተጋሉ፡፡ ገዳማቸውን ስንደግፍ በዓታቸውን ስናጸና በረከታቸው ያድርብናል፡፡

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444

12 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.