Logo
Getu Temesgen
ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚሰደዱ የዱር እንሰሳት የመመለስ ዕድላቸው እየቀነሰ መምጣቱ ተገለጸ
#ethiopia | ባለፉት ሦስት ዓመታት በተደረገ ጥናት በተለያዩ ምክንያቶች ‎ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚሰደዱ የዱር እንሰሳት ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ዕድላቸው ከቀደሙት ዓመታት የዚህኛው ዓመት መቀነሱ መረጋገጡን፤ የኢትዮጵያ የዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል።

‎በፓርኮች ውስጥ የሚኖሩ የዱር እንሰሳት ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚሰደዱት በሕገ-ወጥ አደን፣ በሕገ-ወጥ የሰዎች አሰፋፈር እና መሰል ሁኔታዎች ነው ተብሏል።

‎የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰሎሞን መኮንን፤ የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን በምሳሌነት በማንሳት፤ ከፓርኩ ወደ ደቡብ ሱዳን ተሰደው የሚመለሱ የዱር እንሰሳት ከዚህ ቀደም ከነበረው በከፍተኛ መጠን መቀነሱን ለአሐዱ ተናግረዋል።

‎ችግሩን ለመፍታት "ኤፒ አፍሪካ ፓርክ" የተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን የገለጹም ሲሆን፤ እንደ ሀገር የዱር እንስሳት የጥበቃ ሽፋንን ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

‎"ዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት ነው" ያሉም ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ለተፈጥሮ ሀብቶች የተለየ ትኩረት በመስጠት ተጠቃሚነቷን ማስፋት እንዳለባት አሳስበዋል።

በተጨማሪም ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የዱር እንሰሳት ላይ የሚፈጸመውን ሕገ-ወጥ አደን ጨምሮ ደህንነታቸውን ለመጠበቅ እና የቱሪዝት መስህብነታቸውን እንደጠበቁ እንዲቆዩ ለማገዝ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለሥልጣን እና በክልሎች የሚተዳደሩና ከአጠቃላይ የሀገሪቱ መሬት የቆዳ ስፋት 10 ነጥብ 6 ከመቶ የሚሆነውን የሚይዙ፣ በዓለም የመረጃ ቋት የሚታወቁ 87 ፓርኮችና ጥብቅ ቦታዎች የሚገኙ ሲሆን፤ በተለያዩ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ችግሮች ምክንያቶች በፓርኮቹ የሚገኙ የዱር እንሰሳት ቁጥር እየተመናመነ እንደሚገኝ ይገለጻል፡፡ #ahaduradio

1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.