Logo
Getu Temesgen
ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች እና ደላሎች ያመረትነውን ምርት በአግባቡ እንዳንሸጥ እያደረጉን ነው ሲሉ አርሶአደሮች ቅሬታቸውን ገለጹ
#ethiopia | ‎ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች እና ደላሎች ያመረትነውን ምርት በአግባቡ እንዳንሸጥ እያደረጉን ነው ሲሉ በኦሮሚያ ክልል ሆለታ ከተማ የመደጉዲ ቀበሌ አርሶአደሮች ቅሬታቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል።

‎አርሶአደሮቹ፤ "ያመረትናቸውን እንደ ቆስጣ፤ ሰላጣ ፤ጥቅል ጎመን እና የመሳሰሉ የአትክልት ምርቶችን በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ በመላክ ስንሸጥብንቆይም አሁን ላይ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች እና ደላሎች ጣልቃ እየገቡ ከልክ በታች እንድንሸጥ እየተገደድን ነው" ብለዋል።

‎"ተደራጅተን ምርቱን ወደ አዲስ አበባ ስንልክ ሕገ-ወጥ ደላሎች ጣልቃ እየገቡ ከመደበኛ ነጋዴዎች ጋር በመነጋገር አትክልቱ ቶሎ እንዳይሸጥ ስለሚያደርጉ አትክልቱ እንዳይበላሽ ስንል ብቻ ሳንፈልግ በግማሽ ቀንሰን ለመሸጥ እንገደዳለን" ሲሉም ተናግረዋል።

‎በዚህም አርሶአደሮች "እንደዚህ አይነት ምርት ለምናቀርብ ሰዎች የገበያ ቦታ እንዲመቻችልና፤ ወደ ከተማ ወስደን ለመደበኛ ነጋዴዎች እንድናስረክብ አስቻይ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይገባል" ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ሕገ-ወጥ ደላሎችንና ነጋዴዎችን የሚመለከተው አካል እንዲቆጣጠር ጠይቀዋል።
‎
‎አሐዱም የአርሶአደሮችን ቅሬታ በመያዝ የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮን ጠይቋል።

በዚህም በኦሮሚያ ንግድ ቢሮ የሰብል ምርቶች ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ጉቱ ተመስገን በሰጡት ምላሽ፤ "በሆለታ ከተማ አርሶአደሮች ምርታቸውን የሚያቀርቡበት የክልሉ ንግድ ቢሮ ያዘጋጀው ቦታ አለ" ብለዋል።

ዳይሬክተሩ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ አርሶአደሮችም ወደ ከተማዋ ገብተው ምርታቸውን እንዲያቀርቡ በ5 ትልልቅ የገበያ ቦታዎች ለሁሉም ክልሎች በኮታ ተለይቶ ከአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ጋር እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
‎
‎"የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ በሰጠን ኮታ መሠረት ዓመቱን ሙሉ በቀጣይነት ለአዲስ አበባ ከተማ ማቅረብ የሚችሉ አርሶአደሮች ለይተን እየሰራን ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

‎በክልሉ የሚገኙ ሕገ-ወጥ ደላሎችን እና ነጋዴዎችን ሙሉ በሙሉ ከመቆጣጠር አንፃር ክፍተቶች ቢኖሩም፤ ሕገ-ወጥነትን ለመቀነስ ንግድ ቢሮው በርካታ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። #ahaduradio

1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.