Logo
Getu Temesgen
መድኃኒትን በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችል አዲስ የዲጂታል መተግበሪያ ይፋ ሆነ
‎
‎#ethiopia | ታካሚዎች በሐኪም የታዘዘላቸውን መድኃኒት ለማግኘት ከፋርማሲ ወደ ፋርማሲ ከመዘዋወር የሚያድን «ሄሎ ፋርማሲ» የተሰኘ ዲጂታል መተግበሪያ ይፋ ሆነ። መድረኩ ታካሚዎችን ከመድኃኒት አቅራቢ ፋርማሲዎች በቀጥታ በማገናኘት ጊዜንና ወጪን ለመቆጠብ ያለመ ነው።
‎
‎የ«ጤና ፈርስት ፕላስ» መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም አሰፋ እንደገለጹት፣ ተጠቃሚዎችበሞባይል መተግበሪያ የሚፈልጉትን መድኃኒት መመዝገብ የሚችሉ ሲሆን፣ ስማርት ስልክ የሌላቸው ደግሞ በነፃ የ6037 የስልክ መስመር በመደወል ጥያቄያቸውን ማቅረብ ይችላሉ ብለዋል። በመድረኩ ከ560 በላይ ፋርማሲዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ የታካሚዎችን ጥያቄ ተከትሎ መድኃኒቱ በእጃቸው መኖሩን በማረጋገጥ ምላሽ ይሰጣሉ።
‎
‎መተግበሪያው ተጠቃሚዎች አቅራቢያቸው ያለውን ፋርማሲ እንዲያውቁ፣ ርቀቱን እንዲመለከቱና የጉግል ማፕ አቅጣጫን በመጠቀም በቀላሉ እንዲደርሱ ያግዛል። በተጨማሪም ፋርማሲዎች የተለያዩ የዋጋ ቅናሽ አማራጮችን እንዲያቀርቡ በማስቻል ተጠቃሚዎች በዋጋና በቦታ ረገድ የተሻለ ምርጫ እንዲያደርጉ ዕድል ይፈጥራል። በመድረኩ መመዝገብ የሚፈልጉ ፋርማሲዎችም የቅድመ ክፍያ ሳይጠየቁ የምዝገባ መረጃቸውን በማስገባት ወደ ስርዓቱ መቀላቀል እንደሚችሉ አቶ አብርሃም ገልጸዋል።
‎
‎በቴሌ-ሕክምና ዘርፍ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሠራ የቆየው «ጤና ፈርስት»፣ በአዲሱ መድረክ አማካኝነት ከሕክምና ምርመራ ጀምሮ እስከ መድኃኒት ግዥ ድረስ ያለውን ሂደት የበለጠ ቀላልና ፈጣን ለማድረግ እየሠራ መሆኑ ተገልጿል። አገልግሎቱ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሚገኙ ዜጎች እና በመላው አለም በአረብ አገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተደራሽ እየሆነ እንደሚገኝ መተግበሪያው በተዋወቀበት መድረክ ላይ ገልጸዋል።
‎
‎ጌትነት ተመስገን
‎📷 ከበደ መክብብ
‎
‎#hellopharmacy #tenafirstplus #digitalhealth #healthcareinnovation #pharmacyservices #ethiopia #ethiopiantechnology #telemedicine #digitaltransformation

1 day ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.