Logo
Getu Temesgen
ቪዛና ኢታ ሶሉሽንስ ለ148 ሺህ ነጋዴዎች ዲጂታል ክፍያ ሊያደርሱ ነው
‎
‎#ethiopia | ቪዛ (Visa) እና ኢታ ሶሉሽንስ (ETTA Solutions PLC) በኢትዮጵያ እስካሁን ከተጀመሩ የነጋዴ ዲጂታይዜሽን ፕሮግራሞች ትልቁ እንደሆነ የተገለጸውን የጋራ ፕሮግራም አስጀምረዋል። ፕሮግራሙ በመላ አገሪቱ ለ148 ሺህ ነጋዴዎች ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ክፍያ መቀበያ አገልግሎት ለማዳረስ ያለመ ነው።

‎በስትራቴጂካዊ አጋርነቱ መሠረት 148 ሺህ የዞሪያ (Zoorya) ክፍያ መቀበያ መሳሪያዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ዘመናዊ የሽያጭ ቦታ (POS) ተርሚናሎች ለነጋዴዎች ይሰራጫሉ። ይህም በአዲስ አበባ ከሚገኙ ትላልቅ የችርቻሮ መደብሮች ባሻገር በአካባቢ ሱቆች፣ በገበያ ነጋዴዎች፣ በምግብ ቤቶች፣ በፋርማሲዎችና በትንንሽ ንግዶች የዲጂታል ክፍያ ተቀባይነትን ያሰፋል።
‎
‎ነጋዴዎች ቪዛ (Visa) ካርዶችን በንክኪ ብቻ መቀበል የሚያስችላቸው ሲሆን፣ ካርድ፣ የኪውአር (QR) ኮድ፣ የሞባይል ገንዘብና ከሂሳብ ወደ ሂሳብ የሚደረጉ ክፍያዎችንም በአንድ መሳሪያ መቀበል ይችላሉ። መሳሪያዎቹ የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ አሰጣጥንና የንግድ ሥራ አስተዳደርን ከክፍያ አገልግሎት ጋር በማጣመር ነጋዴዎች የሽያጭና የክምችት መረጃዎቻቸውን በቀላሉ እንዲያስተዳድሩ ያግዛሉ።
‎
‎የኢታ ሶሉሽንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የዞሪያ ፔይ (ZooryaPay) ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ተመስገን ገብረሕይወት፣ አጋርነቱ የኢትዮጵያን የንግድ ሥርዓት ወደ ንክኪ አልባ ዲጂታል ክፍያ ለማሸጋገር የሚያግዝ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ኩባንያው ባለፈው ዓመት ብቻ ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የንግድ ልውውጥ በሥርዓቶቹ በኩል ማስኬዱን ጠቁመዋል።
‎
‎አዲሱ ፕሮግራም ከክፍያ መቀበያ በተጨማሪ ለነጋዴዎች የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሳደግም ያለመ ነው። በነጋዴዎች የግብይት ታሪክ ላይ በመመስረት የብድር ብቁነት መገለጫ እንዲዘጋጅላቸው የሚያደርግ ሲሆን፣ ኢታ ሶሉሽንስ ከኦፕታሲያ (Optasia) ጋር ባለው አጋርነት አማካይነት ነጋዴዎች ከአጋር ባንኮች የሥራ ማስኬጃ ብድር ለማግኘት የሚያመች ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ ነው።
‎
‎የኢታ ሶሉሽንስ መድረክ አውቶሜሽን፣ የክፍያ መቀበያ፣ ኢ-ኮሜርስና የብድር አገልግሎትን በአንድ ሥርዓት የሚያገናኝ ሲሆን፣ ይህም ነጋዴዎች ሽያጫቸውን ከማስተዳደር ጀምሮ ክፍያ እስከመቀበልና የፋይናንስ ዕድል እስከማግኘት ድረስ ያለውን ሂደት በተቀናጀ መልኩ እንዲያከናውኑ ያስችላል።
‎
‎ፕሮግራሙ በመጀመሪያ በአዲስ አበባ የሚጀምር ሲሆን፣ በቀጣዮቹ ወራት ወደ መላ ኢትዮጵያ እንደሚስፋፋ ተገልጿል። በዚህም በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ተቀባይነትን ከማስፋት ባሻገር ትንንሽና ጥቃቅን ንግዶች የግብይት መረጃቸውን በመጠቀም ወደ መደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲቀርቡ ለማድረግ ዕድል ይፈጥራል።
‎
‎ጌትነት ተመስገን
‎📷 ከበደ መክብብ
‎
‎#ethiopia #visa #ettasolutions #zoorya #zooryapay #digitalpayments #digitaltransformation #fintech #financialinclusion #contactlesspayments #merchantdigitization

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.