Logo
AHADU RADIO FM 94.3
የጉራጌ ክትፎና የየም ብሔረሰብ ባህላዊ የመድሀኒት ለቀማን ጨምሮ 11 ቅርሶችን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

የጉራጌ ክትፎ እና የየም ብሔረሰብ ባህላዊ የመድሀኒት ለቀማን እንዲሁም ያሆዴ፣ መሳላ፣ ሄቦ እና ሴራ የተሰኙትን የተለያዩ ብሔረሰቦች ዘመን መለወጫ በዓል ጨምሮ 11 ቅርሶች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) እንዲመዘገቡ እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለአሐዱ አስታውቋል።

በክልሉ በዩኔስኮ የተመዘገበው የጢያ መካነ ቅርስ በርካታ ጥቅሞችን እያስገኘ እንደሚገኝ የጠቆሙት የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ ደግነህ ቦጋለ አንድ ቅርስ ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ ሲመዘገብ በርካታ ጎብኚዎችን እንደሚስብ አንስተዋል።

በክልሉ ቋሚ፣ ተንቀሳቃሽና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ያጠቃለለ በአጠቃላይ 11 ቅርሶች በዩኒስኮ እንዲመዘገቡ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ከእነዚህ መካከል የሀድያ ዘመን መለወጫ ያሆዴ፣ የከምባታና ጠንባሮ ዘመን መለወጫ መሳላ፣ የየም ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ሄቦ፣ እና የሀላባ ዘመን መለወጫ ሴራ እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

ከእነዚህ በተጨማሪም የጉራጌ ክትፎ አዘጋጃጀትና ጥበብ ሥርዓት እንዲሁም የጆካ ጊጫ የሚሰኘው የጉራጌ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት እና የየም ብሔረሰብ ባህላዊ የመድሀኒት ለቀማ በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ ክልሉ በክልልነት ከተደራጀ በኋላ ባለፉት 3 ዓመታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራበት መቆየቱን አስገንዝበዋል።

ምክትል ሀላፊው አክለውም እነዚህ ቅርሶች አሁን አሁን ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታና የሚዳስሱ መረጃዎች ተሰብስበው በፋይል መልክ እየተቀመጡ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

ቅርሶች እንክብካቤ እና ጥበቃ እንዲደረግላቸው በዩኔስኮ ቢመዘገቡ የተሻለ ነው ተብሎ እንደሚወሰድ አንስተዋል።
ይህንን ተከትሎም ከታችኛው መዋቅር የሚቀርቡ በርካታ ጥያቄዎች መኖራቸውን ገልፀው ቢሮው ለፌደራል እና ተጠሪ ለሆኑ ተቋማት ጥያቄዎችን በማቅረብ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በስፍራሽ ደመላሽ

#አሐዱ_ሬዲዮ_94 .3
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ Photo
2 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.