Logo
AHADU RADIO FM 94.3
ከ30 ዓመት በላይ ያገለገሉ የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው ዕገዳ በጊዜያዊነት መነሳቱ ተገለጸ

ከ30 ዓመት በላይ አገልግሎት የሰጡ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ጅቡቲ እንዳይገቡ ተጥሎ የቆየው ዕገዳ በጊዜያዊነት መነሳቱን የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ተሽከርካሪዎቹ ረጅም ጊዜ ያገለገሉ በመሆናቸው አገልግሎት እንዳይሰጡ ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር ይታወሳል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኔ ዘርዑ ለአሐዱ ሬድዮ እንዳስታወቁት መንግስት በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን የሚያበረታታ የፖሊሲ ለውጥ በማድረጉ ረጅም ዓመታት ያስቆጠሩ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ለመቀነስ እየተሰራ ይገኛል።

ፌደሬሽኑ በብድር አዳዲስ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ለማስገባት ጥረት እያደረገ በመሆኑ በቆዩት ላይ ተጥሎ የነበረው ዕገዳ በጊዜያዊነት ተነስቶ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ገልጸዋል።

ረጅም ዓመታት አገልግሎት የሰጡ ተሽከርካሪዎችን ያለበቂ ዝግጅት ከዘርፉ ማስወጣት ተገቢ አለመሆኑን አቶ ብርሃኔ ጠቁመዋል።

አክለውም፤ ለውሳኔው ተግባራዊነት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ በጥናት የተረጋገጠ መረጃ ባይኖርም ከ14 እስከ 15 ሺህ የሚገመቱ የጭነት ተሽከርካሪዎች እንደሚገኙ ይታመናል።

በተመስገን ተጋፋው

#አሐዱ_ሬዲዮ_94 .3
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
3 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.