Logo
AHADU RADIO FM 94.3
የማቲዮስ ወንዱ ፋውንዴሽን መስራች ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የማቲዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን መስራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንዱ በቀለ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ዛሬ መስከረም 24 ቀን 2019 ዓ.ም. ረፋድ ከዚህ ዓለም ተለይተዋል።

አቶ ወንዱ በቀለ በኢትዮጵያ በካንሰር በሽታ ቁጥጥር እና በሕፃናት ሕክምና ድጋፍ ዙሪያ የሚሰራው "ማቲዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን" (የቀድሞው ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ) መስራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ።

በሙያቸው የቢዝነስ አስተዳደር ባለሙያ የሆኑት አቶ ወንዱ በቀለ፣ የበጎ አድራጎት ሥራቸውን እንዲጀምሩ ያደረጋቸው ልጃቸው ሕፃን ማቲዎስ ወንዱ በደም ካንሰር (Leukemia) ሕመም ምክንያት በሕፃንነቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ነበር።

የልጃቸውን ሕልፈት መታሰቢያ በማድረግ ሚያዝያ 9 ቀን 1996 ዓ.ም (በ2004 እ.ኤ.አ) ድርጅቱን መሠረቱ።

ተቋሙ በካንሰር ለተያዙ አቅም የሌላቸው ሕፃናትና ወላጆቻቸው የምክር፣ የመጠለያ፣ የሕክምና ቁሳቁስ እና የፋይናንስ ድጋፍ ይሰጣል።

በተጨማሪም፤ የካንሰር ተጋላጭነትን ለመቀነስ ጥብቅ የትንባሆ ቁጥጥር ሕጎች በሀገሪቱ እንዲወጡ ከጤና ሚኒስቴር እና ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመሆን ከፍተኛ የፖሊሲ ሙግት አድርገዋል።

አሐዱ ሬድዮ አቶ ወንዱ በቀለ ህልፈት የተሰማውን ሐዘን እየገለጸ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ይመኛል።

#አሐዱ_ሬዲዮ_94 .3
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
3 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.