Logo
AHADU RADIO FM 94.3
አሸንድዬ፣ ሻደይ፣ ሶለል እና የአገው ፈረሰኞች በዓላት በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ በጥናት ተለይተው ለኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን መላካቸው ተገለጸ

የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የአሸንድዬ፣ ሻደይ እና ሶለል በዓላትን "የሰሜን ኢትዮጵያ የልጃገረዶች በዓላት" በሚል፣ የአገው ፈረሰኞች ባህልን ደግሞ "የአገው ፈረስ ባህል" በሚል ስያሜ በዩኔስኮ በማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ ለማስመዝገብ በጥናት መለየቱን አስታውቋል።

ቢሮው ለጥናቱ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን አጠናቅቆ ለኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ማስረከቡን ለአሐዱ ሬድዮ ገልጻል።

የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ እምቢያለ ለአሐዱ ሬድዮ እንዳስታወቁት፣ ቅርሶቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታወቁ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችን በመሳብ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ገቢ ያስገኛሉ።

ቅርሶቹ በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ ጥረት የሚደረገው ጥንታዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉና ዓለም አቀፍ የጥበቃ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ መሆኑንም አብራርተዋል።

አቶ አበበ አክለውም፤ "እነዚህ ባህሎች የአብሮነት እና የሰላም ውርስ በመሆናቸው በሕዝቦች መካከል ያለውን እርቅና ሰላማዊ አብሮነት ለዓለም የሚያሳዩ ናቸው" ብለዋል።

የአማራ ክልል በቱሪስት ሀብት የታደለ በመሆኑ፣ ቅርሶችን በማጉላትና የገቢ ምንጭ በማድረግ ረገድ በትኩረት እንደሚሠራም አጽንኦት ተሰጥቶበታል።

በደረጄ መንግስቱ

#አሐዱ_ሬዲዮ_94 .3
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
5 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.