Logo
ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal
ኢራን በኃይል አንገዛም ስትል ለድርድር በሩን ክፍት ማድረጓን አስታወቀች፡፡

 
የኢራን ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር፣ ኢራን በማስፈራራትና በኃይል ጫና የምትመራ አገር እንዳልሆነች አስታውቀዉ አሜሪካ የሰነዘረችውን የ“ማጥፋት” ማስፈራሪያ ተቃውመዋል።

አክለውም ቴህራን “የኃይል ቋንቋን” እንደማትቀበል ገልጸዋል። በተመሳሳይ ግን ኢራን የጦርነቱን መቋጫ ለማምጣት ለውይይትና ለዲፕሎማሲ በሩን ክፍት ማድረጓን አሳውቃለች።
በአሜሪካ በኩል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ ከኢራን ጋር የጦርነቱን መቋጫ የሚያመጣ ስምምነት ላይ ለመድረስ ረጅም የድርድር ሂደት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ሆኖም ዋሽንግተን የዲፕሎማሲ አማራጩን ብቻ ሳይሆን የጦር አማራጯንም እንደምትጠብቅ አስጠንቅቀዋል፡፡  ይህም ሁለቱ ወገኖች ለውይይት ፈቃደኛ ቢሆኑም፣ በመካከላቸው ያለው አለመተማመን እንደቀጠለ ያሳያል።
 

በጦርነቱ ተጽዕኖ የአሜሪካ ወታደሮችም ከባድ ጫና እየተጋፈጡ መሆኑ ተገልጿል። የአሜሪካ ባሕር ኃይል እንዳስታወቀው፣ አብርሀም ሊንከን በተባለው የጦር መርከብ ቡድን ውስጥ ቢያንስ ስምንት ራስን የማጥፋት ሙከራዎች ተመዝግበዋል።የባሕር ኃይሉ ወታደሮቹ የሕክምናና የምክር ድጋፍ እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።
 

በሌላ በኩል፣ የኢራን የደህንነት ኃላፊ ሞህሰን ሬዛዪ፣ የአሜሪካን የአየር መንገድ ማዕቀብ የሚተገብሩ አገሮችን አስጠንቅቀዋል። እነዚህ አገሮች በኢራን ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ካስፈጸሙ፣ የአየር ማረፊያዎቻቸው መስተጓጎል ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ነዉ የተናገሩት ።
በዚህ መልኩ የኢራንና የአሜሪካ ግጭት ከጦር ሜዳ አልፎ ወደ አየር መጓጓዣና ዓለም አቀፍ ግንኙነት እየተስፋፋ መሆኑ ተመልክቷል።
 

ቴህራን በአንድ በኩል ለአሜሪካ ጫና እንደማትሸነፍ እያሳየች በሌላ በኩል ግን የጦርነቱን መቋጫ ለማምጣት የድርድር በርን ክፍት አድርጋለች። ዋሽንግተንም ድርድርን ብትጠብቅም፣ የጦር አማራጭን እንደማትተው አስታውቃለች። ይህም ቀጣዮቹ የዲፕሎማሲ ውይይቶች የግጭቱን አቅጣጫ ለመወሰን ወሳኝ እንደሚሆኑ እንደሚያመላክት አልጃዚራ አስነብቧል፡፡
 
ቤዛዊት አራጌ
#ዳጉ_ጆርናል
13 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.