Logo
AHADU RADIO FM 94.3
የ'ኤልኒኖን' ተጽዕኖ ለመቋቋም እና የዱር እንስሳትን ለመታደግ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ እንደሆነ ተገለጸ

መስከረም 13 ቀን 2019 ዓ.ም.  (አሐዱ ሬዲዮ) የ'ኤልኒኖ' የአየር ንብረት መዛባት በብሔራዊ ፓርኮችና ብርቅዬ የዱር እንስሳት ላይ የሚያደርሰውን አደጋ ለመከላከል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን እንደተናገሩት፣ ስራው በዋና ዋና የዱር እንስሳት መጠለያዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየተከናወነ ይገኛል።

ድርጊቱ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ተጽዕኖዎች እንዳይቋረጥ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በተለይም በበጋ ወቅት በድርቅ በሚጠቁ አካባቢዎች የሚገኙ የዱር እንስሳትን ለመታደግ ሰፊ ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ተገብቷል።

በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በቅርቡ በተዘረጋው የ50 ኪሎ ሜትር አጥር ምክንያት እንስሳቱ ወደ ወንዝ ወርደው ውሃ እንዳያጡ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ከወንዙ በቧንቧ ውሃ የመሳብ ስራ እየተከናወነ ነው።

ከፍተኛ የውሃ እጥረት በሚያጋጥምበት የስንቅሌ ቆርኬዎች መጠለያ ከሲዳማ ክልል ጋር በመተባበር የውሃ መስመር በመዘርጋት የውሃ ገንዳዎችን የመስራት ስራ ተጀምሯል ተብሏል።

ባለፈው የድርቅ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቶ በነበረው የቦረና ብሔራዊ ፓርክም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ተመሳሳይ የውሃ አቅርቦት የማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

የተፈጥሮ ሀብቱን ለመጠበቅ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት አመራሮች እና ከሕብረተሰቡ ጋር የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ እንደሚገኝም አቶ ሰለሞን መኮንን አብራርተዋል።

ወልደሐዋርያት ዘነበ
#አሐዱ_ሬዲዮ_94 .3
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ፌስቡክ ገጽ፡- https://web.facebook.com/a...
ቴሌግራም ገጽ፡- https://t.me/ahaduradi
14 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.