Logo
EBC
የመደመር እሳቤ ያበበበት ታሪካዊ ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ በብሪክስ ፕላስ እና አዲሱ የጂኦፖለቲካ አሻራ
*************************

ኢትዮጵያ በ1923 ዓ.ም የመንግሥታት ማህበር (League of Nations) አባል ለመሆን ያደረገችው እልህ አስጨራሽ ጥረት፣ በመቀጠልም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራችና አንጋፋ ሀገር በመሆን ያስመዘገበችው ደማቅ ታሪክ የዲፕሎማሲዋ መሰረት ነው።

ዛሬ በዚህ ምዕተ ዓመት ደግሞ ታሪካዊ ቀጣይነቱን ያረጋገጠ ሌላ ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ አሻራን ማሳረፍ ተችሏል።

ከታኅሣሥ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ የብሪክስ ፕላስ ሙሉ አባል በመሆን የዓለም አቀፉ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ዋና ተዋናይነቷን አረጋግጣለች።

ይህ ታላቅ ስኬት በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፉክክር እና ትብብርን በሚያስታርቀው የመደመር እሳቤ የተገበረው የላቀ የመሪነት ዲፕሎማሲ ፍሬ ነው።

አካሄዱ ወዳጅ እና ጠላት ከሚል ጠባብ ፍረጃ የተላቀቀ፣ አጋርነትን ማብዛት ላይ ያተኮረ እና የሀገራችንን ሉዓላዊነት በጽኑ መሰረት ላይ ያቆመ ነው።

ከ40 በላይ ሀገራት አባል ለመሆን ወረፋ በያዙበት በዚህ መድረክ ኢትዮጵያ ቀዳሚ መሆኗ የዲፕሎማሲ ክብደቷን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

የብሪክስ መሪዎች የኢትዮጵያን ታላቅ ህልምና ስትራቴጂካዊ ቦታ ተረድተው አባል እንድትሆን የመረጡበት ቁልፍ ምክንያቶች በርካታ ናቸው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ለቀይ ባህር እና ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች ቅርብ በመሆኗ የብሪክስ ሀገራት በቀጣናው ያላቸውን ተፅእኖ ለማስፋት ምቹ መድረክ ትሆናቸዋለች።

በተጨማሪም ሰፊ የገበያ እድል እና የሰው ኃይል ባለቤት መሆኗ፣ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ፣ ከነባሮቹ አባላት (ቻይና፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካ) ጋር ያላት ጠንካራ የሁለትዮሽ አጋርነት እና የባለብዙ ዋልታ (Multipolar) ዓለም ራዕይ በጥቂቱ ተጠቃሽ ናቸው።

ገለልተኛ የውጭ ፖሊሲ የምትከተለው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፋይናንስና ፖለቲካ ተቋማት ፍትሃዊ መሆን አለባቸው ብላ የምታምነው ጽኑ አቋም ከብሪክስ መሠረታዊ ራዕይ ጋር ሙሉ በሙሉ ይጣጣማል።

ይህ አባልነት የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ፍላጎታችንን ያማከለ ከመሆኑም በላይ በቀጣናችን ተፎካካሪዎቻችን ሊፈጥሩ የሚችሉትን የወደፊት መሰናክል አስቀድሞ በብልሃት ያመከነ ዲፕሎማሲያዊ ብስለት ነው።

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አስራ አንዱ የብሪክስ አባል ሀገራት የዓለማችንን 49 በመቶ የህዝብ ቁጥር፣ 36 በመቶ የቆዳ ስፋት፣ 40 በመቶ የዓለም አቀፍ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) እና 23 በመቶ የሚሆነውን የዓለም አቀፍ ንግድ ይወክላሉ።

ከምዕራባውያኑ የቡድን ሰባት (G7) ስብስብ ጋር ሲነጻጸር የብሪክስ ፕላስ የበላይነት እጅግ አስገራሚ ነው። የብሪክስ ፕላስ ኢኮኖሚ 88 ትሪሊየን ዶላር ወይም የዓለማችንን 45 በመቶ ሲሸፍን፣ የጂ-7 ሀገራት ግን 62 ትሪሊየን ዶላር ወይም 31 በመቶ ላይ ይገኛል።

ከህዝብ ብዛት አንጻር ብሪክስ ፕላስ ከ3.3 ቢሊየን በላይ ህዝብ (ከዓለም አጠቃላይ ህዝብ ግማሹን) ሲያቅፍ፣ ጂ-7 ግን 800 ሚሊየን ህዝብ ብቻ አለው። ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ እና ዋና ዋና የንግድ ማዕከላትም በዚሁ ስብስብ እጅ ይገኛሉ።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ 37 በመቶ የውጪ ንግድ እንቅስቃሴ የሚከናወነው ከብሪክስ ሀገራት ከነበሩትና አዳዲስ አባላት ከሆኑት እንደ ቻይና፣ ህንድ፣ ሳውዲ አረቢያ እና ኢንዶኔዥያ ጋር ነው።

አባልነቱ ብሪክስ ፔይ (BRICS Pay) በተባለው አዲስ የክፍያ ስርአት እና በሀገር ውስጥ ገንዘብ የመገበያየት እድልን በመክፈት የውጪ ምንዛሬ እጥረታችንን ለመቅረፍ ትልቅ በር ይከፍታል።

በተጨማሪም 100 ቢሊየን ዶላር ካፒታል ያለው አዲሱ የልማት ባንክ (New Development Bank) ከምዕራባውያን የፖለቲካ ቅድመ ሁኔታ ነጻ የሆነ አማራጭ የልማት ፋይናንስ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከዚህ አባልነት ጋር ሲቀናጅ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚያመጣ የታመነበት ተስፋ ነው።

"ለጽናት፣ ለፈጠራ፣ ለትብብር እና ለዘላቂነት" በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው 18ኛው የብሪክስ መሪዎች ጉባኤ ላይ ሀገራችን በዓለም አቀፍ የንግድና የአየር ንብረት ድርድር ላይ ድምጿን ከፍ አድርጋ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን አረጋግጣበታለች።

የብሪክስ ፕላስ ማዕበል የዓለማችንን የጂኦፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ትርክት እየቀየረ ባለበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ የታሪካዊ ሽግግሩ ተመልካች ሳይሆን ዋና ተዋናይ መሆን ችላለች።

መንግሥት በመደመር እሳቤ አጋር በማብዛት እና ብሄራዊ ጥቅምን በማስቀደም ያረጋገጠው ይህ የዲፕሎማሲ ስኬት መላው ኢትዮጵያዊ የሚኮራበት እና የሚደግፈው የጋራ ድል ነው።

በሜሮን ንብረት
#ethiopia #ebc #bricsplus #medemer #ethiopiandiplomacy #geopolitics

22 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.