Logo
EBC
ከጎረቤት አልፎ ወደ ሀገር የዘለቀው የኢትዮጵያውያን የማጋራትና የደግነት እሴት
**************

መስከረም ሲጠባና አደይ አበባ የኮረብታዎችን ማዕረግ ለብሶ ሲያብብ፣ ህፃናት በውብ ባህላዊ አልባሳታቸው አምረው "አበባ አየሽ ወይ፣ ለምለም" እያሉ በየደጃፉ በእንቁጣጣሽ ዝማሬ አዲሱን መንፈስ ያበስራሉ።

አባወራዎች የሸማኔውን ጋቢ ተጎናጽፈው፣ እናቶች በባህል ቀሚስ ተውበው፣ መላው ቤተሰብ ማዕድ በጋራ ታድመው በዓሉን በደስታ ያደምቁታል።

አዲስ ዓመት በሀገራችን የዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን፤ ዘመድ ከዘመድ የሚጠያየቅበት፣ ያለው ለሌለው እጁን ዘርግቶ የሚያካፍልበት እና የደግነት እሴታችን የሚንጸባረቅበት ታላቅ ማኅበራዊ ሁነት ነው።

በኢትዮጵያውያን ባህል "ለብቻ መብላት" ነውር ተደርጎ ይታያል። ይህ የደግነት እሴት በተለይ በበዓላት ወቅት ከቤት አልፎ ወደ እምነት ተቋማትና የሕዝብ አደባባዮች ዘልቆ ይስተዋላል።

በየቤተእምነቱ ደጅ እና በየአደባባዩ አቅም የሌላቸውና ጧሪ አልባ ወገኖች እንዲሁም መንገደኞች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ማዕድ ይላክላቸዋል።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ ይህ ማዕድ በማጋራት አብሮ የመደሰት እሴት ከቤተሰብ፣ ከጎረቤትና ከአካባቢ አልፎ ወደ ሀገር ደረጃ በመሻገሩ ፍቅርን እና መተማመንን በማጠናከር ላይ ይገኛል።

አዲሱ ዓመት የማካፈል ደግነታችን፣ የገበታ አብሮነታችንና ትስስራችን ተጠናክሮ ሀገራዊ መግባባት የሰፈነበት እንዲሆን እንመኛለን።

መልካም አዲስ ዓመት!

በልዩ እሸቱ
#ethiopia #newyear #ethiopiannewyear #sharing #ebc

25 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.