Logo
FBC
የነገዋ ኢትዮጵያ - በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምህዳር

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ)የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪካዊ የነጻነትና የሉዓላዊነት አርማ ባለቤት ነው።
የአድዋ ድል የዚህ እውነት አንዱ ማሳያ ነው። ዛሬ ላይ የሉዓላዊነት ትርጓሜ ከዚህም ተሻግሮ የሳይበር ምህዳርን እና የዲጂታል ደህንነትን መቆጣጠርን ጨምሯል።

ኢትዮጵያ ይህንን የዘመኑን ጥሪ በመቀበል ብሔራዊ የሳይበር ሉዓላዊነቷን አረጋግጣለች። መረጃዎቿን በሀገር ውስጥ ዘመናዊ ዳታ ማዕከላት በማከማቸት እውነተኛ የመረጃ ሉዓላዊነትን በተግባር እውን ማድረግ ችላለች።

ለዘላቂ ልማት የሰውን ልጅ አእምሮ ማበልጸግ ወሳኝ ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በ"5 ሚሊዮን ኢትዮ ኮደርስ" ግዙፍ ፕሮጀክት ታላቅ የትውልድ ግንባታ በማካሄድ፣ ዘመኑን የዋጀ የተማረ የሰው ሀይል በማፍራት የጎላ ስራ መስራት ተችሏል።

ለዘመናት የቆየውን የተንዛዛ ቢሮክራሲያዊ ማነቆ ለመስበር ዲጂታል አገልግሎቶች በስፋት እየተተገበሩ ናቸው። በተለያዩ ቦታዎች በተበታተኖ መልኩ ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች ከ70 በላይ በሆኑ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች እየተሰጡ ይገኛሉ።

ስማርት ፖሊስ ጣቢያ ማቋቋምን ጨምሮ በፍትህ ተቋማት ዲጂታላይዝድ አሰራር መዘርጋቱ የወንጀል መከላከልና የፍትህ አሰጣጡን አዘምኗል። ከ41 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በፋይዳ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ተመዝግበው ዘመናዊ አሰራር ውስጥ ገብተዋል፡፡ የዲጂታል ግብር አሰባሰብም የሀገር ውስጥ ገቢን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጓል።

በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ አዳዲስ እመርታዎች ታይተዋል። የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ መቋቋሙ ለምርምር ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። በምጥን ግብርና ቴክኖሎጂ አርሶ አደሩ የአፈርና የዝናብ ሁኔታን አስቀድሞ በማወቅ ምርታማነቱን ማሳደግ ችሏል።

ስታርት አፕ ኢትዮጵያ ወጣቶች ሀሳባቸውን ወደ ንግድ እንዲቀይሩ ምቹ ምህዳር ፈጥሯል። ስማርት ስልኮችን በሀገር ውስጥ የመገጣጠም ስራ መጀመሩ ሀገሪቱን ከሸማችነት ወደ ፈጣሪነትና አምራችነት እያሸጋገራት ይገኛል። የ4ጂ እና 5ጂ ኔትወርክ ተደራሽነት እየሰፋ ነው። የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ግቦች በመሳካት ላይ ናቸው።

እነዚህ ሁለንተናዊ የቴክኖሎጂ ስኬቶች የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን እያደረጓት ይገኛሉ። ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የነገ ህልም ብቻ ሳይሆን ዛሬ በገሀድ የምንኖረው እውነት መሆኑን በተጨባጭ መረጃዎች አይተናል።

አዲሷ ኢትዮጵያ በማይናወጥ ጠንካራ መሰረት ላይ ቆማለች። የነገዋ ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ሙሉ በሙሉ የበለጸገች፣ በራሷ ልጆች አቅም የምትተዳደር እና ለዜጎቿ ሁሉ የምትመች ታላቅ ሀገር እንደምትሆን የጀመርናቸው ስራዎች ይመሰክራሉ።

በቴዎድሮስ ኮሬ

26 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.