Logo
Getu Temesgen
በአቶ ታዬ ደንደአ ላይ ተጥሎ የነበረው የአራት ዓመት የጽኑ እስራት ውሳኔ በሰበር ሰሚ ችሎት ጸደቀ
#ethiopia | የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የቀድሞው የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ላይ የታዘዘውን የአራት ዓመታት የእስር ቅጣት ሙሉ በሙሉ ማጸናቱን አስታወቀ።

ችሎቱ በአዲስ አበባ በዋለው ሰበር ችሎት በአቶ ታዬ ደንደአ በኩል የቀረበውን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ በታችኛው ፍርድ ቤት ተበይኖ የነበረውን ውሳኔ አጽንቶታል።

አቶ ታዬ በመጀመሪያ ደረጃ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት በሚል በተመሠረተባቸው ክስ የሰባት ዓመት እስር ተፈርዶባቸው የነበረ ቢሆንም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ይግባኝ ቅጣቱ ወደ አራት ዓመት ዝቅ እንዲል ተደርጎ ነበር።

ይሁን እንጂ በተሰጠው ውሳኔ ላይ ቅሬታ የነበራቸው አቶ ታዬ አምስት የመከራከሪያ ነጥቦችን በማንሳት ለፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም ችሎቱ የቀረበውን ጥያቄ ሳይቀበለው ቀርቷል።

የአቶ ታዬ ደንደአ ባለቤት ወይዘሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃል ባለቤታቸው የመሣሪያውን መገኘት ባያስተባብሉም ከሌሎች ዜጎች እኩል የመዳኘት መብት እንደተከለከሉ እና ካቀረቧቸው አምስት ተከላካይ ምስክሮች መካከል የሁለቱ ብቻ ቃል ተሰምቶ ውሳኔ መሰጠቱን በቅሬታነት ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አቃቤ ሕግ ይግባኝ ባሰማበት ተጓዳኝ የክስ ነጥብ ላይ ፍርድ ቤቱ ለጥቅምት 17 ቀን 2019 ዓ.ም. ቀጣይ ቀጠሮ ሰጥቷል።
#ፍትሕ #ችሎት #ዜና #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.