Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የሚኒሶታ ጤና መምሪያ በግዛቲቱ በሚገኙ የሜክሲኮ ምግብ ቤቶች ውስጥ ከሚቀርበው ሃላፒኖ የሚባለው የቃሪያ ዓይነት (የሜክሲኮ ቃሪያ) ጋር የተያያዘ የ'ሳልሞኔላ ጃቪያና' ወረርሽኝን እየመረመረ መሆኑን አስታወቀ። መምሪያው እስካሁን 110 የተረጋገጡ የሳልሞኔላ ታማሚዎች መመዝገባቸውን ገልጿል።

የጤና ባለስልጣናት ህመሙ ከተከሰተባቸው ሰዎች መካከል 84ቱን ያነጋገሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 75 በመቶ የሚሆኑት ከሰኔ 14 እስከ ሀምሌ 14 ባለው ጊዜ ውስጥ 'ቺፖትሌ' በተባለው ታዋቂ ምግብ ቤት የተመገቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ቀሪዎቹ ደግሞ በሌሎች የሜክሲኮ ምግብ ቤቶች መመገባቸውን ተናግረዋል። ወረርሽኙን ተከትሎ ቺፖትሌ በሚኒሶታ ከሚገኙ በርካታ ቅርንጫፎቹ ሃላፔኖ ቃሪያዎችን ማንሳቱን አስታውቋል።

የቺፖትሌ ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ፣ "ሊከሰት ስለሚችለው ወረርሽኝ እንደሰማን ወዲያውኑ የክትትል ስርዓታችንን በመጠቀም ሃላፔኖ ቃሪያው የተሰራጨባቸውን ምግብ ቤቶች ለይተናል፤ ለጥንቃቄ ሲባልም የተጠረጠሩትን ምርቶች ከምግብ ቤቶቻችን በማስወገድ ከሌሎች አምራቾች በተገኙ ቃሪያዎች ተክተናል" ብለዋል። በሚኒሶታ ጤና መምሪያ የምግብ ወለድ በሽታዎች ክፍል ከፍተኛ ኤፒዲሚዮሎጂስት ካርሎታ ሜዱስ በበኩላቸው፣ ቺፖትሌ ከምርመራው ጋር በተያያዘ መረጃዎችን ከመስጠት ጀምሮ የተጠረጠሩትን ቃሪያዎች ለማስወገድ የወሰደውን ፈጣን እርምጃ በማንሳት የተቋሙን ሙሉ ትብብር አድንቀዋል።

የጤና መምሪያው ወረርሽኙ አሁንም እንደቀጠለ ለማወቅ ጊዜው ገና መሆኑን ቢገልጽም፣ ቺፖትሌ በወሰደው ፈጣን እርምጃ ምክንያት በድርጅቱ ላይ ስጋት እንደሌለው አስታውቋል። ሆኖም የተበከለው ቃሪያ በሌሎች ምግብ ቤቶች አሁንም እየቀረበ ከሆነ ወረርሽኙ ሊቀጥል እንደሚችል እና በቀጣይ ቀናት ተጨማሪ ታማሚዎች ሊመዘገቡ እንደሚችሉ ስጋቱን አጋርቷል።

ወረርሽኙን በፍጥነት ለመቆጣጠር የታማሚዎች መረጃ እጅግ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ካርሎታ ሜዱስ፣ የጤና ባለሙያዎች ምርመራቸውን የሚያካሂዱት ጥቆማ በደረሳቸው ታማሚዎች ላይ በመደወል በመሆኑ፣ ህብረተሰቡ ለሚደረጉ የስልክ ጥሪዎች ምላሽ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

1 day ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.