Logo
EBC
የትግራይ ወጣቶች እውነተኛ ፍላጎት ሰላም ነው - የምክክር ጉባኤ ተሳታፊው ወጣት
************************************

ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የቆዩ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ያለመ ታሪካዊ መድረክ ነው።

የትግራይ ክልልን በመወከል በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው እየተሳተፈ ያለው ወጣት፣ በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በማንሳት የክልሉ ወጣቶች ዋና ፍላጎት ሰላም መሆኑን ይናገራል።

በምክክር ጉባኤ ተሳትፎው ለሀገር ግንባታ ይጠቅማል የሚለውን ሀሳብ በነጻነት እያቀረበ እንደሚገኝ ወጣቱ ገልጿል።

ጦርነት በትግራይም ሆነ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች የወጣቶችን ሕይወት ከመቅጠፍ እና ማኅበራዊ ውድቀትን ከማስከተል ውጭ ያተረፈው ነገር እንደሌለ ጠቅሷል።

ተምረው ሀገር ሊገነቡ፣ ሥራ ፈጥረው ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ሊረዱ የሚችሉ ወጣቶች የጦርነት ሰለባ መሆናቸው ሀገርን ለከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ እንደሚዳርግ አንስቷል።

የትግራይ ወጣቶችን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ሲናገርም፣ ወጣቱ ወደ ጦርነት አውድማ እየገባ ያለው በገዛ ፍላጎቱ ሳይሆን በግዳጅና በአፈሳ እንደሆነ ገልጿል።

የክልሉ ወጣቶች እውነተኛ ፍላጎት ሰላም፣ ትምህርት፣ የሥራ ዕድል እና የተረጋጋ ሕይወት እንጂ ወደ አላስፈላጊ ውጊያ መግባት አለመሆኑን የገለጸው ተመካካሪው፣ ሀሳባቸውን በነጻነት የሚገልጹበት እና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን በራሳቸው የሚወስኑበት ምህዳር ሊመቻችላቸው እንደሚገባ ጠቁሟል።

በፖለቲካው ምህዳር ሰፊ ልዩነት ቢኖርም እንኳ ይህን ልዩነት በጠብመንጃ ሳይሆን በውይይት ጠረጴዛ ዙሪያ በመቀመጥ እያጠበቡ መሄድ እንደሚቻል ተሳታፊው አስምሮበታል።

ይህ ዓይነቱ ችግሮችን እና ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በምክክር እና በሀሳብ የበላይነት የመፍታት ባህል በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ሊጎለብት እንደሚገባ ተናግሯል።

በሔዋን ጌታቸው
#ethiopia #nationaldialogue #tigray #youth #peace #ebc

7 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.