Logo
FastMereja
ጊፍት ትሬዲንግ 35ኛ ዓመት የምስረታ ኢዮቤልዩውን አከበረ!
#fastmereja :- በኢትዮጵያ በገቢና ወጪ ንግድ ዘርፍ አንጋፋ ከሆኑ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ጊፍት ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር፣ የተመሰረተበትን 35ኛ ዓመት የምስረታ ኢዮቤልዩ በዓል በዛሬዉ እለት አክብሯል።

በንግድ ማህበረሰቡ፣ በመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና በድርጅቱ አመራሮች በተገኙበት በዚህ መርሃ-ግብር ላይ ኩባንያው ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ከግማሽ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ያቀረበ ሲሆን፣ በቀጣይም ወደ አግሮ-ኢንዱስትሪ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሸጋገር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ይፋ አድርጓል።

ድርጅቱ ይፋ ባደረገው እቅድ መሠረት በአዳማ እና ሞጆ ከተሞች መካከል በሚገኘው የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ፍሪ ዞን ውስጥ 7,527.54 ካሬ ሜትር ቦታ መረከቡን ገልፀዉ ቦታው ከጅቡቲ ኮሪደር እና ከሞጆ ደረቅ ወደብ አቅራቢያ የሚገኝ በመሆኑ፣ የገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴውን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳልጠው የተገለጸ ሲሆን፤ የአካባቢው የዲዛይን ስራ ተጠናቆ ወደ ግንባታ ምዕራፍ መሸጋገሩ ተመልክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ኩባንያው እሴት በተጨመረባቸው የግብርና ምርቶች ዘርፍ መሰማራት የጀመረ ሲሆን፣ በተለይም በድፍድፍ የአቮካዶ ዘይት ማምረት እና በከባድ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች አስመጪነት ዘርፍ ለመግባት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል።

የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ለማሳደግ እና የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለማጠናከር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ በቤንች ሸኮ ዞን የጥቁር አዝሙድ እርሻ መጀመሩን የጠቆመው ጊፍት ትሬዲንግ፤ በቀጣይ ስድስት ወራት ውስጥ 300 ሄክታርየቡና እርሻ መሬት ተረክቦ ወደ ምርት እንደሚገባ አስታውቋል።

ከ50 ዓመታት በፊት በመርካቶ በታዋቂው የቢዝነስ ሰው በአቶ ገብረኢየሱስ ኢጋታ ሲማ በትንሽ የችርቻሮ ሱቅ የተጀመረው ይህ የንግድ እንቅስቃሴ፣ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ወደ ገቢና ወጪ ንግድ በማደግ ለዛሬው ግዙፉ ጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ (ጊፍት ሪል እስቴት፣ ጊፍት ኮንስትራክሽን፣ ጊፍት ብረታ ብረት፣ ጊፍት ፕሮፐርቲ እና ጊፍት ቱር ኤንድ ትራቭል) መፈጠር መሰረት መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም B-29 የልብስ ሳሙና፣ የሮድ ስቶን የተሽከርካሪ ጎማዎች፣ የጂንዳል ቆርቆሮዎች፣ የብረትና የኬሚካል ምርቶችን ጨምሮ በርካታ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ለሀገር ውስጥ ገበያ በማስተዋወቅ ረገድ ኩባንያው የነበረው ሚና ከፍተኛ እንደነበር ተገልጿል።

ኩባንያው እ.ኤ.አ በ2030 በኢትዮጵያ በቡና፣ ቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ እና ቅመማ ቅመም ላኪነት ከግንባርቀደም 5 ኩባንያዎች አንዱ የመሆን ራዕይ ሰንቋል።

12 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.