Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የካናዳ ፍርድ ቤት በ4 ኤርትራዊያን ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አሳለፈ፡፡ በካናዳ ካልጋሪ ከተማ የሚገኘው ፍርድ ቤት ዳኛ 4 ኤርትራዊያን በቀረበባቸው የረብሻ፣ ጦር መሳሪያ መያዝና ድብደባ ክስ ጥፋተኞች ሆነው መገኘታቸውን ገለፁ፡፡ ዳኛው ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማችን ውስጥ ከተከሰቱት ረብሻዎች በሙሉ ትልቁ›› በሚል የገለፁት ይህ ድርጊት የተፈፀመው እ.ኤ.አ በ2023 ሴፕቴምበር ወር ነበር፡፡ በወቅቱ በፖለቲካ ልዩነት ያላቸው ሁለት የኤርትራዊያን ቡድኖች በፋልኮን ፕላዛ እርስ በእርሳቸው ፀብ ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል፡፡

ይህ ድርጊት ከተፈፀመ ሶስት አመት የሆነው ቢሆንም ዳኛው ግን የተፈጠረው ሁከት እንደሆነና 4ቱ ተከሳሾች ጥፋተኛ መሆናቸውን ማረጋገጥ ከባድ አለመሆኑን በውሳኔያቸው ገልፀዋል፡፡ ዳኛው ሎይድ ሮበርሰን በንባብ ባሰሙት 2 ሰአታትን በፈጀ ውሳኔያቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ ያሳለፉባቸው አማኑኤል ክፍለግዚ፣ ያሚን እቁበዮሀንስ፣ ገብኪዳን ሀይለማሪያምና ሙሴ እስጢፋኖስ ናቸው፡፡

ለፍርድ ቤት በቀረበው ሰነድ መሰረት በወቅቱ የነበረው ፀብ 10 ደቂቃ የፈጀ ቢሆንም 97 እንጨትና ቱቦዎች፣ 118 ድንጋዮችና 18 ጠርሙሶች በሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ ተወርውረዋል፡፡ ፖሊስ ፀቡን ለማብረድ ወደ200 ያህል የፖሊስ አባላትን ከማሰማራቱም በላይ በርካታ የጭስ ጋዝና ከ2000 በላይ የሚያቃጥሉ ድቡልቡል ጥይቶችን እንደተጠቀመም ለፍርድ ቤት የቀረበው ሰነድ ያሳያል፡፡

13 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.