Logo
Ethio telecom
ኩባንያችን የ2018 በጀት ዓመት እና የቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታል እና ከዚያም ባሻገር ስትራቴጂ የመጀመሪያ ዓመት እቅዱን በላቀ ስኬት ማጠናቀቁን በታላቅ ደስታ እናበስራለን!

በ2018 በጀት ዓመት የማህበረሰባችንን ችግሮች የሚፈቱ፣ የኢንተርፕራይዝ ደንበኞችን ውጤታማነት የሚያሳድጉና የሀገራችንን ተወዳዳሪነት የሚጨምሩ በርካታ አገልግሎቶችን አቅርበናል፡፡

በበጀት ዓመቱ 264 ተጨማሪ ከተሞች የ4ጂ LTE አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ሲሆን፤ አጠቃላይ የ4ጂ ተጠቃሚ ከተሞች ቁጥር 1,200 ማድረስ ተችሏል፡፡ በሰባት ከተሞች የ5ጂ ተጨማሪ ማስፋፊያዎችን በማከናወን በአጠቃላይ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከተሞችን ቁጥር ወደ 33 ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡

ኩባንያችን የደንበኞች ቁጥርን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ የቻለ ሲሆን፣ አጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚዎቻችንን ቁጥር 90.12 ሚሊዮን ማድረስ ተችሏል። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተያዘውን ግብ 101.7% በማሳካት ከአቅድ በላይ ስኬታማ አድርጎናል።

በበጀት ዓመቱ 603 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ወደ ስራ የገቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም 195 የሚሆኑት የገጠር አካባቢዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው፤ ተጨማሪ 10.2 ሚሊዮን የኔትወርክ አቅም በመገንባት አጠቃላይ አቅምን ወደ 115.1 ሚሊዮን ማድረስ ተችሏል፡፡

በተጨማሪም 475 አዳዲስ እና የተሻሻሉ ምርቶችና አገልግሎቶች ለግል ደንበኞች፣ ኢንተርፕራይዝ፣ ፊንቴክ፣ ዲጂታል ላይፍስታይል እንዲሁም በአለም አቀፍ የቢዝነስ ዘርፎች ላይ ለገበያ ማቅረብ ተችሏል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ኩባንያችን ጠንካራ የፋይናንስ አፈፃፀም በማስመዝገብ አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢውን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ33.2% ማሳደግ የቻለ ሲሆን፣ 215.82 ቢሊዮን ብር በማግኘትም የያዘውን ዕቅድ 99.7% ስኬታማ አድርጓል። ለዚህ የገቢ ስኬት የዳታና ኢንተርኔት አገልግሎት በ31.1% እንዲሁም የሞባይል ድምፅ አገልግሎት በ23.5% ድርሻ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

በተጨማሪም የኩባንያችን ያልተጣራ ትርፍ (EBITDA) የ51.9% ዕድገት በማሳየት 113.1 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የሥራ ማስኬጃ ትርፍም (Operating Profit) ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ47.5% በመጨመር 92.9 ቢሊዮን ብር መድረስ ችሏል።

የኩባንያችን ቤተሰቦች፣ ደንበኞቻችን፣ የሥራ አጋሮቻችንና ሚዲያዎች በስኬታችን ጉዞ አብሮነታችሁ ስላልተለየን ከልብ እናመሰግናለን!

ለተጨማሪ፡ https://bit.ly/45k6Gjw

14 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.