ኢትዮጵያ ወደ ቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት የምታደርገው ጉዞ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዘመናዊው ዓለም የሀገራት ፉክክር በወታደራዊ ኃይል ወይም በተፈጥሮ ሀብት ብቻ አይወሰንም፡፡
የቴክኖሎጂ አቅም፣ የዲጂታል መሠረተ ልማትና የመረጃ ሉዓላዊነት የሀገራትን የወደፊት እድገት የሚወስኑ ቁልፍ መለኪያዎች ሆነዋል።
ኢትዮጵያም ባለፉት 5 ዓመታት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ያከናወነቻቸው ሥራዎች የዲጂታል ሽግግር መሠረት ጥለዋል፡፡ በ2ኛው ምዕራፍ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ወደ ቀጣዩ የቴክኖሎጂ ዘመን ለማሸጋገር በትኩረት እየሰራች ነው።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ዋና ግብ የመንግሥት አሰራርን ማዘመን፣ የቢሮክራሲ ጫናን መቀነስ፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን ማፋጠንና የዜጎችን የኑሮ ጥራት ማሻሻል ነበር።
በዚህም የቴሌኮም ዘርፉ ለውድድር ተከፍቶ፣ የ4ኛና 5ኛ ትውልድ ኔትወርክ አገልግሎቶች ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲስፋፉ በማድረግ የኢንተርኔት ተደራሽነትን እንዲጠናከር አድርጓል፡፡ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የሚፈጠሩ አዳዲስ ዕድሎችንም አስፍቷል።
የዲጂታል ፋይናንስ ሽግግሩም በሀገሪቱ ውስጥ አዲስ ምዕራፍን የከፈተ ሲሆን÷ የሠራተኞች ደመወዝ፣ የነዳጅ ግብይትና የትራፊክ ቅጣት ክፍያዎች በዲጂታል ስርዓት መፈጸማቸው ግብይቶችን ፈጣን፣ ግልጽና ቀልጣፋ አድርጓል።
በተመሳሳይ ሚሊየኖች በፋይዳ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ተመዝግበው አገልግሎት እያገኙ ሲሆን÷ የፓስፖርት፣ የንግድ ፈቃድና የታክስ አገልግሎቶችን ወደ ኦንላይን ማሸጋገር ጊዜን ከመቆጠብ ባሻገር የሙስና እድሎችንም ለመቀነስ አስችሏል።
የቴክኖሎጂ ሽግግሩ በአገልግሎት ዲጂታላይዜሽን ብቻ አልተወሰነም፤ የ5 ሚሊየን ኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭ የወጣቶችን የቴክኖሎጂ ክህሎት በማሳደግ ለወደፊቱ የዲጂታል ኢኮኖሚ ጠንካራ የሰው ኃይል ለመገንባት አግዟል፡፡ይህም ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ወደ መፍጠርና ማልማት የሚደረግ ስልታዊ ሽግግር መሆኑን ያሳያል።
የዲጂታል ሉዓላዊነቷን ለማጠናከር ከሶፍትዌር ልማት ባለፈ በሃርድዌር ምርት ላይም ትኩረት የሰጠችው ኢትዮጵያ የላፕቶፕ፣ የታብሌትና ሌሎች ዲጂታል መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የፋብሪካ ግንባታ እያከናወነች ትገኛለች።
ከዚህ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም ሩቅ ይመስል የነበረው የድሮን ቴክኖሎጂ ዛሬ በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉ በቴክኖሎጂ ራስን የመቻል አቅም እየጠነከረ መምጣቱን ያመለክታል።
ዲጂታላይዜሽን ያለ ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ሊሳካ እንደማይችል በመገንዘብም ኢትዮጵያ የሕግ፣ የተቋምና የቴክኖሎጂ አቅሟን በማጠናከር የዲጂታል ሥነ ምህዳሯን እየገነባች ትገኛለች።
የተሻሻለው ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ፣ የግል መረጃ ጥበቃና የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሕጎች ለዲጂታል ኢኮኖሚው አስተማማኝ ሕጋዊ መሠረት ፈጥረዋል።
በተመሳሳይ የመከላከያ ሳይበር ማዕከል የሰለጠኑ የሳይበር ኃይሎችን በማፍራት የአገሪቱን ዲጂታል ሀብቶችና ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን ለመጠበቅ አቅሙን እያጠናከረ ይገኛል።
በዚህ መሠረት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የ2025 ስትራቴጂ ቀጣይ ምዕራፍ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ፣ ወደ ቴክኖሎጂ ፈጠራና ወደ ሉዓላዊ የመረጃ ሥርዓት የሚያሸጋግር ብሔራዊ ራዕይ ነው።
ስትራቴጂው የሰው ሰራሽ አስተውሎትን እና ሌሎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በኢኮኖሚ፣ በመንግሥታዊ አገልግሎትና በማኅበራዊ ዘርፎች ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ያለመ ነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የጀመረችው የዲጂታል ጉዞ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ከማስፋት ባለፈ የራሷን ቴክኖሎጂ የምትፈጥር፣ የምታመርትና የምትጠብቅ ሀገር ለመሆን የተጀመረ ስልታዊ ጉዞ መሆኑን በግልጽ አሳይቷል።
የዲጂታል 2030 ራዕይ ጥንካሬ ያላት፣ በቴክኖሎጂ ራሷን የቻለች እና ለወደፊቱ ፉክክር ዝግጁ የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት ጠንካራ መሠረት ይጥላል።
በዮናስ ጌትነት

18 days ago