Logo
FBC
ሰውሰራሽ አስተውሎት፡ የግብርናው አዲስ አጋር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በግብርና ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር መሆኗ የሚታወቅ ነው። በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ኑሯቸውን የሚመሩት በእርሻ ነው።

ሆኖም የአየር ንብረት ለውጥ፣ የተባይ መስፋፋት፣ የገበያ አለመረጋጋት እና የመረጃ እጥረት ዘርፉን አሁንም በፈተና ውስጥ አድርገውታል።

በዚህ መካከል ግን የሰው ሠራሽ አስተውሎት አዲስ ተስፋ ይዞ ብቅ ብሏል።

አንዳንዶች ሰው ሰራሽ አስተውሎትን የሮቦቶች ዓለም እንደሆነ ያስባሉ፤ እውነታው ግን የግብርናን ሥራ ቀላል፣ ፈጣን እና ውጤታማ የሚያደርግ ውጤታማ የመረጃ ሥርዓት ነው።

ሰውሰራሽ አስተውሎት የሰውን ጉልበት የሚተካ ሳይሆን የሚያጠናክር ቴክኖሎጂ ነው።

ይህ ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ደግሞ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ትልቅ እድል ይዞ መጥቷል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት የአየር ሁኔታ መረጃዎችን በመተንተን የዝናብ፣ የድርቅና የሙቀት ለውጦችን አስቀድሞ መተንበይ ይችላል።

ይህም አርሶ አደሮች መቼ እንደሚዘሩ፣ መቼ እንደሚሰበስቡ እና እንዴት ምርታቸውን እንደሚጠብቁ በትክክል እንዲወስኑ ያግዛል።

በሌላ በኩል ቀደም ሲል የእጽዋት በሽታዎችን እና ተባዮችን ለመለየት የግብርና ባለሙያ መጠበቅ ግድ ይል ነበር። ዛሬ ግን በሞባይል ስልክ በተነሳ ፎቶ ብቻ በቴክኖሎጂው በመታገዝ በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ በሽታውን መለየት የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ይህም ተባዮችና በሽታዎች ከመስፋፋታቸው በፊት ፈጣን ርምጃ እንዲወሰድ እገዛ ያደርጋል።

በተጨማሪም ከአፈር ሴንሰሮች የሚሰበስበውን መረጃ በመተንተን ቴክኖሎጂው እፅዋት መቼ ውሃ እንደሚፈልጉ መረጃ በመስጠት የውሃ ብክነት እና ወጪን ይቀንሳል።

የኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በመጠቀም ረገድ በለውጡ ዓመታት በርካታ ተግባራትን አከናውናለች።

ለአብነትም የሰብል እድገትን፣ የምርት መጠንን እና የድርቅ አደጋን ለመገምገም፤ እንደ አንበጣ ያሉ ተባዮችን አስቀድሞ መለየትና ፈጣን ምላሽ መስጠት፤ ለአርሶ አደሮች ስለ አየር ሁኔታ፣ የመዝራት ጊዜ፣ የማዳበሪያ አጠቃቀም እና የሰብል እንክብካቤ መረጃ በዲጂታል መንገድ ማቅረብ ይጠቀሳሉ።

ብዙ የግብርና መረጃዎችን በመተንተን ለፖሊሲ አውጪዎች እና ለውሳኔ ሰጪዎች ትክክለኛ የውሳኔ ድጋፍ መስጠት፣ ግብርናን ለማዘመን፣ የምርት መጠንን ለማሳደግ እና የምግብ ዋስትናን ለማጠናከር በብሔራዊ የሰውሰራሽ አስተውሎት ስትራቴጂ ውስጥ ቅድሚያ ሰጥታለች።

ኢትዮጵያ ሰውሰራሽ አስተውሎትን በግብርናው ዘርፍ በመጠቀም የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቀነስ እና ለአርሶ አደሮች በመረጃ ላይ የተመሠረተ የግብርና አገልግሎት ለማቅረብ እየሰራችበት ትገኛለች፡፡

ሆኖም ግን ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በብቃት ለመጠቀም ያስችል ዘንድ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት፣ የዲጂታል ክህሎት፣ የመረጃ ጥራት እና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት መጠናከር ያስፈልጋል።

በተጨማሪም የግብርናው ስራ በሰውሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ወጣቶች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች እና መንግሥት እንዲሁም ሌሎች አካላት በጋራ እና በቅንጅት ሲሠሩ ይገባል።

በአመለወርቅ ደምሰው

23 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.