Logo
FBC
ፈረንሳይ ከስፔን - የፍጻሜ ተፋላሚ ለመሆን…

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የ2026 የዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት መደረግ ይጀምራሉ፡፡

በዚህም መሰረት ምሽት 4 ሰዓት ላይ ፈረንሳይ ከስፔን የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል፡፡ለዋንጫው ቅድመ ግምት ካገኙት ከሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የአንዳቸው ጉዞ ዛሬ ምሽት የሚያበቃ ይሆናል፡፡

ፈረንሳይ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ እስካሁን ድረስ ከሴኔጋል፣ ኢራቅ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ፓራጓይ እና ሞሮኮ ጋር ተገናኝታ ሁሉንም ጨዋታዎች አሸንፋለች፡፡

በአሰልጣኝ ዲዴ ዴሻምፕ የምትመራው ፈረንሳይ እስከ ሩብ ፍጻሜ ድረስ ባደረገቻቸው ጨዋታዎች 16 ግቦችን ተጋጣሚዎቿ ላይ አስቆጥራ የተቆጠረባት ሁለት ግብ ብቻ ነው፡፡

በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን በኩል ኪሊያን ምባፔ፣ የባሎንዶር አሸናፊው ኦስማን ዴምቤሌ እና ኦሊሴ አስደናቂ ጊዜ እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡

ኪሊያን ምባፔ 8 ግቦችን በማስቆጠር የ2026ቱን የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ደረጃን ከሊዮኔል ሜሲ ጋር በጋራ እየመራ ሲሆን÷ በተጨማሪም ሦስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡

ኦስማን ዴምቤሌ ደግሞ አምስት ግቦችን አስቆጥሮ ሁለት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡

ሌላኛው የብሔራዊ ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ኦሊሴ አምስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለ ሲሆን÷ በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ በርካታ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻቶ በማቀበል ቀዳሚው ተጫዋች ነው፡፡

በ2018 እና 2022 የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚ የነበረችው ፈረንሳይ ለሦስት ተከታታይ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ውድድር የፍጻሜ ጨዋታ ላይ ለመገኘት የምታደርገው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው

ፈረንሳይ በፈረንጆቹ 1998 እና 2018 የዓለም ዋንጫን ያሳካች ሲሆን ÷ ለሦስተኛ ጊዜ በመድረኩ ሻምፒዮን ለመሆን የምታደርገውን ጉዞ ለማጠናከር ትፋለማለች፡፡

ሌላኛዋ ለዋንጫ የተገመተችው ተጋጣሚዋ ስፔን በፈረንጆቹ 2010 በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ማሳካቷ ይታወሳል፡፡

ስፔን በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ እስካሁን ድረስ ከኬፕ ቨርዴ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኡራጓይ፣ ኦስትሪያ፣ ፖርቹጋል እና ቤልጂዬም ጋር የተገናኘች ሲሆን÷ አምስቱን አሸንፋ ከኬፕ ቨርዴ ጋር ብቻ አቻ ተለያይታለች፡፡

ስፔን እስካሁን ድረስ ባደረገቻቸው ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቿ ላይ 11 ግቦችን አስቆጥራለች፤ የተቆጠረባት ደግሞ አንድ ግብ ብቻ ነው፡፡

ለስፔን ብሔራዊ ቡድን በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ አራት ግቦችን ያስቆጠረው እና አንድ ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ ያቀበለው ኦያርዛባል በጨዋታው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡

ተቀይሮ ወደ ሜዳ በመግባት ልዩነት እየፈጠረ የሚገኘው ስፔናዊው ተጫዋች ሜሪኖ በዛሬው ጨዋታ ልዩነት ይፈጥራሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳል፡፡

ስፔን ከ2010 በኋላ በድጋሚ በመድረኩ ለመንገስ የምታደርገውን ጉዞ ለማጠናከር ወደ ሜዳ ትገባለች፡፡

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች አሸናፊ ከእንግሊዝ እና አርጀንቲና አሸናፊ ጋር ለዋንጫው ይፋለማል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

24 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.