Logo
FastMereja
"በአቅም ምክንያት ቤተሰቦቼ ባለመገኘታቸው ከፍቶኛል" የዋንጫ ተሸላሚ ተመራቂ
#fastmereja I ተማሪ ማስተዋል ካሳዉ በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ አካባቢ ተወልዳ እንዳደገች ትናገራለች። የመጀመሪያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንም ደብረታቦር አካባቢ እንደተማረች መረጃዎችን ያጋራችን ሲሆን በትምህርቷ ወቅትም ቤተሰቦቿ አቅም የሌላቸዉ በመሆኑ በርካታ ዉጣ ዉረዶችን ፣ፈተናዎችን ለማሳለፍ ተገዳለች።

የ12ኛ ክፍል ከአጠናቀቀች በኋላ የሪሚዲያል ትምህርቷን ለመከታተል ወደ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ብታመራም ዉጤቷ 49.5 በመሆኑ በ0.5% ዉጤት ሳይመጣላት ቀርቷል።

ዉጤት በመቅረቱ ተስፋ ያልቆረጠችዉ ተማሪ ማስተዋል ካሳዉ ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ በማቅናት በለስ ፓራዳይዝ ኮሌጅ በዲፕሎማ መርሃግብር በፋርማሲ ትምህርት ክፍል በግል ለመማር ትመዘገባለች።

ወደ በረሃ ገነቷ ግልገል በለስ ከተማ ለትምህርት ከሄደች በኋላም ቤተሰቦቿ የፋይናንስ አቅም የሌላቸዉ በመሆኑ ህይወት ዉጣ ዉረድ እንደሆነባት ትገልፃለች።

ትምህርቷን ለማጠናቀቅ የትምህርት፣ የዶርም እንዲሁም የእለት ጉርስ ለማግኜት ከትምህርቷ ጎን ለጎን የቀን ስራ በመስራት ራሷን እያስተዳደረች ትምህርቷን በከፍተኛ ዉጤት ለማጠናቀቅ በቅታለች።

ተማሪ ማስተዋል ካሳሁን የቀን ሰራተኛ በመሆን ለተከታታይ ዓመታት ጊዜዋን እየገፋች የነበረ ሲሆን ዛሬ ሐምሌ 4 ቀን 2018 ዓ.ም (26 A+ እና 16A ) 4.00 በማምጣት የ2 ሜዳልያና የዋንጫ ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች።

የዋንጫና የሜዳልያ ባለቤቷ ተማሪ ማስተዋል ካሳሁን ቤተሰቦቿ አቅም የሌላቸዉ በመሆኑ እሷን ለማስመረቅ የመጣ አንድም ቤተሰብ ግን የሌለ በመሆኑ በጣም እንደከፋትም ትናገራለች።

የበረሃ ሰዉ እጅግ ደግ በመሆኑ አከራዮቿና ጎረቤቶቿ ደስታዋን ለመካፈል በምረቃ ፕሮግራሙ የተገኙ መሆኑን ለመታዘብ ችለናል።

በመጨረሻም በለስ ፓራዳይዝ ኮሌጅ ግልገል በለስ ካምፓስ የቀን ሰራተኛዋ ብርቱና ጀግናዋን ባለ ዋንጫና ሜዳልያ ባለቤቷን ተማሪ ማስተዋል ካሳሁንን በቋሚ ቅጥር እንደፈፀመላት የሚያሳይ የቅጥር ደብዳቤ ዋንጫዉን ስታነሳ በኮሌጁ አካዳሚክ ኮሚሽን በኩል በይፋ የቅጥር ደብዳቤዉ ተሰጥቷታል።

መረጃውን የፋስት መረጃ አጋር ምሳሌ ሚዲያ ከስፍራው አድርሶናል።

26 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.