Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ መዝናኛ ዜና) ታዋቂው ራፐር ጄይ-ዚ (ትክክለኛ ስሙ ሾን ካርተር) የ30ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የኮንሰርት ጉዞውን ከባለቤቱ ቢዮንሴ እና ከልጁ ብሉ አይቪ ካርተር ጋር በመሆን ጀምሯል። ትላንት አርብ፣ ጁላይ 10 የ56 ዓመቱ ራፐር በያንግኪ ስታዲየም ባቀረበው ኮንሰርት፣ በመጀመሪያ ሜሪ ጄ. ብላይጅ የተሳተፈችበትን ታዋቂውን "Can't Knock the Hustle" የተሰኘ ዘፈን ተጫውቷል። በወቅቱም የሜሪ ጄ. ብላይጅን የዘፈን ክፍል ቢዮንሴ ተክታ ያቀረበችው ሲሆን፣ በመድረክ ላይ በልበ ሙሉነት እየተራመደች ዘፈኑን በድንቅ ሁኔታ ተጫውታዋለች። የዘፈኑን ክፍል አጠናቃ ስትጨርስ ጄይ-ዚ "ኦህ፣ መዝፈን ትችላለች እኮ!" ሲል አድናቆቱን የገለጸ ሲሆን፣ እሷም በበኩሏ ለተመልካቹ "ለፍቅረኛዬ ሞቅ ያለ አቀባበል አድርጉለት" በማለት ጄይ-ዚን በፈገግታ አሞካሽተዋለች።

ኮንሰርቱ ሲቀጥል፣ የ14 ዓመቷ ልጁ ብሉ አይቪ "Feelin' It" በተሰኘው የ1996ቱ ዝነኛ ዘፈን ላይ አባቷን በመድረክ ተቀላቅላለች። ብሉ አይቪ በዘፈኑ ማጠቃለያ ላይ የፒያኖ ሰለዋን በብቃት በመጫወት ተመልካቹን ያስደመመች ሲሆን፣ ጄይ-ዚም "ለታዋቂዋ ብሉ አይቪ ካርተር ድምጻችሁን አሰሙ" ካለ በኋላ ከልጁ ጋር ረዘም ላለ ጊዜ ተቃቅፈዋል።

የብሉ አይቪ የፒያኖ ብቃት የታየው፣ ጄይ-ዚ ባለፈው ማርች ወር ለጂኪው (GQ) መጽሔት በሰጠው ቃለ መጠይቅ "አስገራሚ የፒያኖ ተጫዋች" መሆኗን ከተናገረ በኋላ ነው። በወቅቱም "አስተማሪ እንድንቀጥርላት አትፈልግም፤ ስራ እንዲሆንባት አትፈልግም። ነገር ግን ፍጹም የሆነ የድምጽ የመለየት አቅም አላት። አንድን ዘፈን ከሰማች 'እንደገና አጫውተው' ትልና ራሷን ታስተምራለች" ብሎ ነበር። አክሎም፣ "ይህ የተፈጥሮ ተሰጥኦ ነው።... በጣም የምትፈልገውን ነገር ለማድረግ በመታገሏ ኩራት ይሰማኛል። አሁን ከመድረክ ላይ ልናወርዳት የምንችል አይመስለኝም" ሲል ገልጿል።

ብሉ አይቪ ከዚህ ቀደም በ2023ቱ "Renaissance World Tour" እና በ2025ቱ "Cowboy Carter World Tour" ላይ እናቷን በመድረክ ተቀላቅላ ነበር። በ2023ቱ ኮንሰርት ለአንድ ምሽት ብቻ እንድትታይ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ከመጀመሪያው ትርኢቷ በኋላ የተሰጡ አንዳንድ አሉታዊ አስተያየቶችን ተመልክታ፣ የ11 ዓመቷ ታዳጊ ዳግም ለመሞከር ወስና እንቅስቃሴዋን እስክታሻሽል ጠንክራ ሰርታለች።

ለ2025ቱ ኮንሰርት ደግሞ የ13 ዓመቷ ታዳጊ በተሻለ ዝግጁነት ወደ መድረክ ተመልሳ፣ ለሶስት ወራት በተካሄዱ 32 የኮንሰርት ትርኢቶች ላይ ከእናቷ ጋር ስትጨፍር ቆይታለች። በወቅቱም የቢዮንሴን የ2006 "Déjà Vu" ዘፈን የዳንስ እንቅስቃሴ ለብቻዋ በመድረክ መሃል በመጫወት ተመልካቾችን ያስደመመች ሲሆን፣ አድናቂዎችም እንቅስቃሴዋን "Dèjà Blue" በሚል ስያሜ አሞካሽተውታል።

እነዚህ ዝነኛ የጥበብ ጥንዶች ብሉ አይቪን ጨምሮ የ9 ዓመት መንታ ልጆች (ሩሚ እና ሰር) እንዳሏቸው ይታወቃል።

27 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.