Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ማናጀር በሆኑት ማህሌት ሰለሞን ስም የዋስትና መክፈያ በሚል በኦንላይን የሚሰበሰበው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘመቻ ሀሰተኛ (Scam) መሆኑን ቤተሰቦቻቸው አረጋገጡ።
ማህሌት ሰለሞን ከሳምንታት የእስር ቆይታ በኋላ በዋስ መለቀቃቸው ይታወሳል። የተለቀቁትም በአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የዋስትና ገንዘብ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንን የዋስትና ገንዘብ ሙሉ በሙሉ የከፈለው ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በአንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች እና ኦንላይን ላይ "ለማህሌት ሰለሞን የዋስትና ገንዘብ" በሚል ሰበብ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ። ቤተሰቦቻቸው ይህ ድርጊት ፈጽሞ ትክክል እንዳልሆነ እና አታላይነት (Scam) መሆኑን አሳስበዋል።

በአሁኑ ሰዓት ማህሌት ሰለሞን ከእስር ተፈትተው ከቤተሰባቸው ጋር እንደሚገኙና ምንም ዓይነት የገንዘብ እርዳታ ጥያቄ እንዳላቀረቡ ቤተሰቦቻቸው አረጋግጠዋል።

ስለሆነም በዚህ ሀሰተኛ ዘመቻ ተታለው በኦንላይን ገንዘብ የከፈሉ ግለሰቦች፣ ወደ ክሬዲት ካርድ ኩባንያዎቻቸው በመደወል የከፈሉትን ገንዘብ እንዲያስመልሱ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። በተጨማሪም፣ ይህንን አታላይ ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባና ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተላልፏል።

ከማህሌት ጋር አብሮ ታስሮ የነበረው ሌላኛው የቴዲ አፍሮ ጓደኛ የሱፍ፣ ተጨማሪ ክስ ቀርቦበት እስካሁን አለመለቀቁንና የፊታችን አርብ፣ ማህሌት ሰለሞንን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ከቤተሰብ ምንጮች ለመረዳት ተችሏል። ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልን ዝርዝር መረጃዎችን የምናደርስ ይሆናል።

28 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.