Logo
FastMereja
የቀድሞው የፓርላማ አባል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ራሳቸውን ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ማግለላቸውን ይፋ አደረጉ
#fastmereja I ባለፉት 5 ዓመታት (ከ2014 እስከ 2018 ዓ.ም) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት ታዋቂው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፣ የፓርላማ ቆይታቸውን ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ከማንኛውም ቀጥተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ራሳቸውን ማግለላቸውን በይፋ አስታውቀዋል። በትናንትናው ዕለት በተጠናቀቀው የምክር ቤት ዘመን ማግስት ውሳኔያቸውን ያሳወቁት ዶ/ር ደሳለኝ፣ ለጊዜው በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ በአባልነትም ሆነ በደጋፊነት እንደማይሳተፉ ገልጸዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ወደ ፖለቲካው ዓለም ከመግባታቸው በፊት በዩኒቨርሲቲ መምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በጣና ሐይቅ የእንቦጭ አረም መከላከል ንቅናቄ ላይ በአክቲቪዝም እና በሲቪክ ማኅበራት መሪነት በግንባር ቀደምትነት ሰርተዋል። ባለፉት 8 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፓርቲ ምስረታ እስከ ከፍተኛ አመራርነት የተጓዙት ዶ/ር ደሳለኝ፣ ባለፉት 5 ዓመታት ደግሞ የባሕር ዳር ከተማ መራጮችን በመወከል በፓርላማ የነቁ ተቃዋሚ ሆነው አገልግለዋል። በዚህ የፖለቲካ ጉዟቸው ወቅትም ለ45 ቀናት መታሰራቸውን አስታውሰዋል።

በትናንትናው የምክር ቤት ጉባዔ ማጠቃለያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ «አብረን እንስራ» በማለት ለተቃዋሚዎች ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ከጉባዔው በኋላ በተደረገ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዶ/ር ደሳለኝ በሰጡት አስተያየት፣ በ7ኛው ዙር ምርጫ በባሕር ዳር ከተማ ለመወዳደር ቢመዘገቡ ኖሮ ብልጽግና ፓርቲ እጩ ላለማቅረብ ወስኖ እንደነበርና በምክር ቤቱ ቢቀጥሉ ፍላጎታቸው እንደነበር ገልጸውላቸዋል።

ይሁን እንጂ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ የቀረበላቸውን የፖለቲካ ፍላጎት በበጎ ካዩት በኋላ፣ ከ10 ዓመታት ተከታታይ የፖለቲካ ድካም በኋላ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ግሉ ዘርፍ (Startups) በመግባት በሙያቸው ሀገርን ለማገልገልና ለቤተሰባቸው ጊዜ ለመስጠት መወሰናቸውን አስታውቀዋል። ቀጥተኛ የፖለቲካ ተሳትፏቸው ቢያበቃም፣ የአማራን ሕዝብ አንድነትና ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር ያለውን አብሮነት በሚያጠናክሩ እንዲሁም በሀገራዊ የሰላም እና የብሔራዊ ውይይት ጉዳዮች ላይ በሙያቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
#ፖለቲካ

28 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.