Logo
FastMereja
ሙት አንሳ ማር ቅዱስ ሚካኤል ገዳም ለጀመረው የልማት ፕሮጀክት ከ63 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማግኘቱን አስታወቀ!
#fastmereja I የሙት አንሳ ማር ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም የገጠመውን መጠለያ የማጣት ችግር ለመቅረፍና ራሱን ለማስቻል በጀመረው የልማት ፕሮጀክት ገዳሙ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከስድስት ወራት ውስጥ ባከናወናቸው የገቢ ማሰባሰብ ሥራዎች፣ ከ63 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ማግኘት መቻሉን በዛሬዉ እለት የአስተዳደሩ ተወካዮች ገልጸዋል።

በመግለጫው ላይ የካናዳ ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ መርቆሪዮስ፣ የቤተክርስቲያን ሊቃውንትና ጥሪ የተደረገላቸው የሚዲያ ተቋማት ተገኝተዋል።

የገዳሙ አስተዳደር እንዳመለከተው፣ በተለያዩ የቴሌቪዥን ዶክመንተሪዎችና በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት በተደረገው ሰፊ የገቢ ማሰባሰብ ጥረት፦52 ሚሊዮን 640 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ፣11 ሚሊዮን 320 ሺህ ብር የሚገመት የዓይነት (የቁሳቁስ) ድጋፍ መሰብሰቡ ነዉ የተገለፀዉ።

ይህ የተገኘው ድጋፍ የልማት ፕሮጀክቱን የመጀመሪያና ሁለተኛ ምዕራፎች ከ65 በመቶ በላይ ለማሳካት ያስቻለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የእናቶች በዓት (የመኖሪያ ክፍል) እና የእንግዳ ማረፊያ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ እናቶች አገልግሎት ማግኘት መጀመራቸው ተጠቅሷል።

ከ160 በላይ ገዳማውያን የሚገኙበት ይህ አንድነት ገዳም፣ ከተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች ጋር ተያይዞ ገዳማውያኑ ከብርድና ከዝናብ የሚከላከል መጠለያ አጥተው በከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኙ እንደነበር በመግለጫው ላይ ተስቷል።

ይህንን የህልውና ፈተና በዘላቂነት ለመቅረፍ የተቀረጸው ይህ ፕሮጀክት፤ በጠቅላይ ቤተ-ክህነት ዕውቅና፣ በሐገረ ስብከቱ ፈቃድ እንዲሁም በሊቃነ ጳጳሳት የቅርብ ክትትልና ቡራኬ ከወረዳ ቤተ-ክህነት ጀምሮ በቅንጅት እየተመራ ይገኛል።

የገዳሙ አስተዳደር "ጾም የነፍስ ምግብ ነው፤ ለፈተናም መቋቋሚያ ጥንካሬን ይሰጣል" የሚለውን የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ኃይለ ቃል በመጥቀስ፣ በአሁኑ ወቅት ምዕመናን የሚገኙበት የሐዋርያት ጾም (የሰኔ ጾም) የበረከት ወቅት በመሆኑ፣ የተጀመረው የልማት ሥራ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜ እንዲያገኝ ሕዝበ ክርስቲያኑ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

30 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.