Logo
EBC
ከጊዜያዊ እርካታ ወደ ዘላቂ ከፍታ፡ የማይሻረው የትውልድ አሻራ
***********************
( የዕለቱ መልዕክት)

ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የልማትና የኢኮኖሚ ምዕራፍ በተጨባጭ የሚዳሰሱ ፍሬዎችን እያሳየ ይገኛል። በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ጥቂት ሀገራት ተርታ ቀዳሚ መሆን መቻሏ በየከተሞች የተገነቡ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻዎችና በየአካባቢው የሚታዩት ሜጋ ፕሮጀክቶች ሀገራችንያላትን ተፈጥሯዊ ጸጋና የመስራት ብቃት በተግባር ያሳዩ ናቸው።

ይሁንና ይህ ስኬት ገና የመንገዳችን ጅማሮ እንጂ ፍጻሜያችን አይደለም። ከትናንት የድህነት ልካችን አንጻር የተሻለ ቦታ ላይ መድረሳችን እውነት ቢሆንም ከሚጠበቅብን ግዙፍ ሀገራዊ ስራ ውስጥ ገና አንድ በመቶዉን ብቻ እንዳከናወንን መገንዘብ ይገባል።

ለአንድ ሀገር ትልቁ ስነ-ልቦናዊ አደጋና በሽታ በትንሽ ስኬት መርካት ነው። በትናንሽ ስኬቶች መታወር ወደፊት እንዳንራመድ አግዶ በነበርንበት እንድንቆም ያደርገናል። በመሆኑም አሁን የተጀመሩት ስራዎች ለቀጣዩ ትልቅ ምዕራፍ እንደ ማበረታቻ ምልክት እንጂ እንደ መጨረሻ ማረፊያ ሊወሰዱ አይገባም።

ሀገርን መገንባት ለእለት ፍጆታ የሚደረግ ጊዜያዊ ሩጫ ሊሆን አይገባም። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደሚሉት ሰው በሀገሩ ላይ የሚገነባውና የሚያለማው ለዕለት ፍጆታ ብቻ መሆን የለበትም፤ የምንሠራው ሥራ የሚዘልቅ፣ የሚሻገርና ለልጆቻችን የሚወረስ መሆን አለበት።

በመሆኑም ዛሬ የምንተክለውና የምንገነባው ማናቸውም መሰረተ ልማት በጥራት ላይ የተመሰረተ ለነገው ትውልድ የሚሻገርና የአካባቢውን ባህላዊና ስነ-ልቦናዊ እሴት የጠበቀ “የማይፈርስ አሻራ” ሊሆን ይገባል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለተኛው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገር እንደመሆኗ መጠን አሁን ያለችበት ቦታ የሚመጥናት አይደለም። ወደሚገባት ታላቅ ከፍታ ለመድረስ የጋራ እይታ፣ የተገለጠ ራዕይ እና የማየት ብቃት ያስፈልገናል። በተለይም በምግብ ራስን መቻል፣ በበጋ ስንዴ ማምረት እና የኤሌክትሪክ ኃይልን ማስፋፋት የህልውና ጉዳዮች እንጂ ምርጫዎች ሊሆኑ አይችሉም።

ይህን ልማት የሚሸከም ጤናማ ማኅበራዊ ስነ-ምኅዳር መፍጠር ግን ቀዳሚው የቤት ስራ ነው። በተለይም የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ አካባቢዎች ማኅበረሰብ ታማኝነትን፣ አስተማማኝ ሰላምን፣ ጽዳትና አረንጓዴነትን እንደ መርህ ሊይዟቸው ይገባል።

የአንድ ቀን የሌብነትና የክፋት ተግባር የአመታትን በጎ ስም በአንድ ጀንበር ያጠለሸዋል። ቱሪስት ንብረቱ ቢጠፋበት እንኳን ተፈልጎ የሚመለስበት የታማኞች ምድር መሆን ቀጣይ ኢንቨስትመንትን የሚስብ ትልቁ ሀብታችን ነው።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የሕዝቦች አንድነትና ትብብር ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያ የብዙ ብሔረሰቦች ውብ ስብስብ ነች። አንዱ ብሔር ከሌላው እንደማይበልጥና ሁሉም እኩል መሆናቸውን አምኖ መቀበል የስልጣኔ መጀመሪያ ነው።

"እኔ እበልጣለሁ፣ ከእኔ ውጪ" የሚለው የትዕቢት ስሜት፣ አካባቢያዊና ብሔር ተኮር ሽኩቻዎች እንዲሁም የፖለቲከኞች የከፋፍለህ ግዛ አጀንዳዎች ለዘመናት በድህነት አቆይተውናል። መበላለጥ መለካት ያለበት በብሄርስም ሳይሆን በተግባርና በስራ ብቻ ነው። አንዱ አካባቢ ሲለማ ሌላው የሚደሰትበት፣ የትም ቦታ የሚመጣን ሰራተኛና ባለሀብት እንደ እራስ ወገን አቅፎ የሚያስተናግድ ሰፊ ልቦና ሲኖረን የሀገራችን ብልጽግና ይፈጥናል።

የሀገር ዕድገትና ትውልድን ማሻገር በተግባር እንጂ በባዶ ንግግርና በልመና አይመጣም። ዓለም አቀፋዊ እውነታው የሚያሳየንም አስቀድመው የተዘጋጁ ሀገራት ጥቅማቸውን እንደሚያስከብሩና ያልተዘጋጁት ደግሞ ሳይነኩ የሚንኮታኮቱ መሆኑን ነዉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳመለከቱትም አሁን ያለው ትውልድ በታሪክ አጋጣሚ የድህነትን መጥፎ አሻራ ተሸክሞ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ይህ ድህነት ወደሚቀጥለው ትውልድ እንዳይሻገር ራሳችንን ክደን፣ ለልጆቻችን ዘላቂ መሠረት የመጣል ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን።

ፈተናዎችና ወደ ኋላ የሚስቡ እጆች ቢኖሩም በመልካም እሳቤና በትጋት የሚሰሩ ኃይሎች ማሸነፋቸው አይቀሬ ነው።
በማንኛውም መመዘኛ እየወደቀ ካለ ሀገር ይልቅ እያደገ ካለ ሀገር ጋር መጓዝ ይመረጣል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ማደግ የጀመረች እና ከፍተኛ ሥራ የምትሻ በመሆኗ የምናፈስሰው ላብና የምናሳየው አንድነት ነገ ለትውልድ የሚተርፍ ታላቅ ሀገር ያጸናል።
ስንሰራም ሆነ ስንተባበር ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገው ትውልድ በሚሻገር አሻራ ላይ ይሁን።

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.