Logo
EBC
የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ሲጠናቀቅ ከተማዋን በምስራቅ አፍሪካ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ የሚያደርግ ፕሮጀክት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
***********************

ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከመንግሥት ድጋፍ ባለፈ የሁሉንም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ እገዛና ትብብር እንደሚሹ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በተካሄደው የሀዋሳ የሐይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የአጋርነት መድረክ ላይ በመገኘት ይህንን ትልቅ ሀገራዊ ራዕይ የመጋራት ዕድል ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ሀዋሳ ማራኪ ሐይቋን ጨምሮ ልዩ ተፈጥሯዊ ጸጋዎች የተቸሯት ከተማ መሆኗን አውስተዋል። ይህንን ስጦታ መጠበቅና ማልማት የጋራ ታሪካዊ ኃላፊነታችን ነው ብለዋል።

የተጀመረው የሐይቅ ዳርቻ ልማት የውበት ሥራ ብቻ ሳይሆን ሰፊ የቱሪዝም፣ የኢኮኖሚ፣ የሥራ ፈጠራና የአካባቢ ጥበቃን ያቀፈ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አስገንዝበዋል።

ታላላቅ ፕሮጀክቶች በመንግሥት ጥረት ብቻ ሊሳኩ ስለማይችሉ የሕዝባችን፣ የግሉ ዘርፍ፣ የምሁራንና የዳያስፖራው ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት የሚደረገው ድጋፍ ከገንዘብ ባሻገር እውቀትን፣ ልምድንና በጎ ተጽዕኖን ማካተት ይኖርበታል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የከተማዋን የመዝናኛ፣ የንግድና የመኖሪያ ሥፍራነት ወደ ላቀ ምዕራፍ በማሸጋገር ሀዋሳን በምስራቅ አፍሪካ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ እንደሚያደርጋትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ጠቁመዋል።

ለዚህ ትልቅ ራዕይ መሳካት እያንዳንዱ ዜጋ በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በጉልበቱ የሚያበርክተው አስተዋፅዖ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.