Logo
EBC
የቢሮክራሲውን ማነቆዎች የሚገታው የኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽን
*********************

(የዕለቱ መልዕክት)

የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ባልተቀላጠፈበት እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በሌለበት ስለ ተገልጋይ እርካታ ማውራት ከንቱ ድካም ነው።

በሀገራችን ለረጅም ዘመናት የቆየው እና የዜጎችን እንግልት ሲያበዛ የኖረው “ዛሬ ሂድ፤ ነገ ና” የሚለው አሰልቺ ቢሮክራሲ፣ የሕዝብን ሮሮ ከመጨመሩ ባለፈ የሙስና አዙሪት መፈልፈያ ሆኖ መቆየቱ የአደባባይ ምስጢር ነው።

ይህንን ሥር የሰደደ ማነቆ ለመፍታት ቴክኖሎጂን እንደ ዋና መፍትሔ መውሰድ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኗል።

ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ እና ወጣት የሰው ኃይል እንዲሁም የመንግሥትን ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት በመጠቀም፣ ቴክኖሎጂውን ለሕዝብ ተጠቃሚነት እና ለኢኮኖሚ ሽግግር በስፋት እያዋለችው ትገኛለች።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በዘርፉ የተመዘገቡት ስኬቶች የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን ከማሳካት ባለፈ፣ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚያቀልሉ፣ ጊዜን እና ገንዘብን የሚቆጥቡ ትልልቅ ተስፋዎችን አብስረዋል።

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተቀረጸው እና በይፋ ሥራ የጀመረው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተንቀሳቃሽ አውቶቡስ ስምሪት አንዱ ነው።

ይህ በአፍሪካ ፈር ቀዳጅ የሆነ አሠራር የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማግኘት በየቢሮው እና በየደረጃው በሚገጥሙ የቢሮክራሲ ሰንሰለቶች የመጉላላት እና በፀሐይም በዝናብም የመንከራተትን ዘመን በዘላቂነት የሚቀይር አዲስ ምዕራፍ ነው።

በልዩ ሁኔታ በተዘጋጁ ንጹሕ ኢነርጂ በሚጠቀሙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ የተመሠረተው ይህ አገልግሎት፤ የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ፣ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (TIN)፣ የንግድ ፈቃድ፣ የመንጃ ፈቃድ፣ የተሽከርካሪ ታርጋ፣ የነዋሪነት መታወቂያ ዕድሳት፣ የልደት ምዝገባ እንዲሁም የመንገድ ፈንድ እና የኤሌክትሪክ ቅድመ-ክፍያ አገልግሎቶችን ጨምሮ ስምንት ዋና ዋና የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ጣራ ሥር ይዞ ወደ ማኅበረሰቡ ደጃፍ መጥቷል።

የዚህ የዲጂታላይዜሽን ስኬት ትልቁ ፋይዳ የአገልግሎት አሰጣጥን ከማቀላጠፍ ባለፈ ሙስናንና የአሠራር ብልሹነትን በተጨባጭ መግታቱ ላይ ነው።

ተንቀሳቃሽ አውቶቡሶቹ ከዋና ዋና የፌዴራል ተቋማት የመረጃ ማዕከላት ጋር በቀጥታ የተገናኙ መሆናቸው፣ በውስጣቸውም ዲጂታል የሰዎች ወረፋ ማስተናገጃ፣ የክትትል ካሜራዎች እና የተለዋዋጭ ዲጂታል ክፍያ አማራጮች መካተታቸው አሠራሩን ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት ያደርገዋል።

ይህ ዓይነቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አዲስ ስምሪት በመንግሥት አገልግሎት ላይ የሚታየውን አሰልቺ ቢሮክራሲ በመቀነስ፣ ሕገ ወጥ ደላሎችን እና ብልሹ አሠራሮችን ከአምራቹ ማኅበረሰብ ትከሻ ላይ ያወርዳል። የአገልግሎት አሰጣጥ ሲፋጠን የሚቆጠበው ጊዜ እና ጉልበት ደግሞ በቀጥታ ወደ ምርታማነትና ወደ ሀገር ሀብት ይቀየራል።

ይሁን እንጂ ይህ የተጀመረው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ይበልጥ ውጤታማና ዘላቂ እንዲሆን የዜጎች እና የሚመለከታቸው አካላት ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

የቆየውን ተቋማዊ እና ግለሰባዊ ልምምድ ቀይሮ በፈገግታና በታማኝነት ማገልገል ቀላል ባይሆንም፣ ቴክኖሎጂው ግን ይህንን የሥራ ባህል ለውጥ እያፋጠነው ይገኛል። በመሆኑም ዜጎች እነዚህን ዘመናዊና ምቹ አገልግሎቶች በባለቤትነት ስሜት በመጠቀም፣ የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት በመሆን ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ሊቆጥቡ ይገባል።

በሌላ በኩል፣ የአመራር አካላት እና የሚመለከታቸው ተቋማት ይህ አመርቂ ጅምር ይበልጥ እንዲስፋፋ፣ መሠረተ ልማቱ እንዲጠናከር እና ኢትዮጵያውያን ባሉበት ስፍራ ሆነው በሞባይላቸው ሙሉ አገልግሎት የሚያገኙበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ በትጋት ሊሠሩ ይገባል።

ቴክኖሎጂ የሀገር ብልጽግና ምሰሶ ከመሆኑም በላይ የዜጎችን ክብር የሚመልስ መሣሪያ በመሆኑ፣ የአገልግሎት ማነቆዎችን የመስበር ይህ አመርቂ ጅምር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል
#ethiopia #ebc #digitalethiopia #mesob #digitalization

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.