Logo
FBC
ሰላም! እንደምን አደራችሁ?

ሀገር የምትሰራው...

ሀገር የምትገነባው በአንድነት፣ በመተማመን እና በጋራ ኃላፊነት ነው፡፡ ሀገር ማለት ከመልክዓ ምድሩ ባሻገር የሕዝቦች ታሪክ፣ ባህል፣ ትውፊት፣ ሕልም እና የወደፊት ትውልድ ተስፋ በአንድነት ተሰናስለው የሚገኙበት ነው፡፡

ዛሬ የምናደርገው ትንሽ መልካም ተግባር የነገዋን ኢትዮጵያ ይቀርጻል። ስለዚህ "ኑ ሀገር እንስራ" የሚለው መልዕክት ለሁሉም ዜጋ የሚቀርብ የሀገር ግንባታ ጥሪ ነው። ልማት ከመንግሥት ብቻ አይጠበቅም፤ ከእያንዳንዱ ዜጋ ቅንነት፣ ታታሪነት፣ ሕግን ማክበር እና ለጋራ ጥቅም መስራት ይጀምራል።ይህን አገላለጽ በተግባር አሁን በኢትዮጵያ ካለው ሁኔታ ጋር ማያያዝ ስለሚያስፈልግ የሚከተለውን እንመልከት።

የለውጡ መንግሥት ከመጣ ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ኢኒሼቲቭ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመሠረተ ልማት፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ አገልግሎት እና በተቋማዊ ማሻሻያዎች ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ለአብነትም የመንገድ ግንባታ፣ የኮሪደር ልማት፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት እና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን መጥቀስ ይቻላል፡፡

እንደ "ገበታ ለሀገር" እና "አረንጓዴ ዐሻራ" ያሉ መርሐ ግብሮች በቱሪዝም፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በተለይ በአረንጓዴ ዐሻራ በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞች መተከላቸው የአካባቢ ጥበቃን በማጠናከር ያለው በጎ አስተዋፅኦ ከአፍሪካ አልፎ ዓለም የመሰከረለት ለውጥ አምጥቷል።

እነዚህ ጥረቶች ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት፣ ለቱሪዝም ማስፋፋት እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ መሠረት ለመሆን ታስበውና ታቅደው መከናወናቸው በሀገሪቱ እድገት አሻራ ያኖሩ ተግባራት ሆነዋል።

በኢኮኖሚው ዘርፍም መንግሥት የግብርና ምርትን ለማሳደግ፣ የኢንዱስትሪ ምርትን ለማበረታታት እና የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሪፎርሞች በመተግበር ተጨባጭ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ብቻ ሳይሆን የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች፣ የግብርና ዘመናዊነት እና የውጭ ንግድ ማስፋፊያ ፕሮግራሞች ተግባራዊ በመደረጋቸው በሀገሪቱ ልማት የመጣው ለውጥ እንደተጠበቀ ሆኖ በእያንዳንዱ ዜጋ ኑሮ መሻሻል የሚታይና የሚጨበጥ አስተዋፅኦ አድርጓል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የኢኮኖሚ እድገት በቁጥር ብቻ ሳይሆን በዜጎች የኑሮ ሁኔታ ላይ በሚያመጣው ተጨባጭ ለውጥ ሊለካ ይገባል የሚል ፅኑ እምነት አለው። በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት፣ የኑሮ ውድነት እና የሥራ አጥነት ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም በቁርጠኝነት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በማህበራዊ ዘርፍ የትምህርት፣ የጤና እና የዲጂታል አገልግሎቶች ማስፋፋት ተስፋ ሰጪ ርምጃዎች ናቸው። የቴክኖሎጂ መስፋፋት ዜጎች አገልግሎትን በፍጥነት እንዲያገኙ እድል ፈጥሯል። መንግሥት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት መፍትሄ ለማበጀትም የሰላም ጥሪን መሰረት ያደረገ የሰለጠነ አካሄድ እየተከተለ ይገኛል፡፡ለሰላማዊ ውይይት ዝግጁ የሆኑ አካላትን ለመቀበልና ለማስተናገድ ግማሽ መንገድ ድረስ ለመጓዝ ዝግጁ መሆኑንም በተደጋጋሚ ከመግለፅ ባለፈ በተግባር አሳይቷል። መንግሥት የሚያቀርበውን የሰላም ጥሪም በተሳሳተ መንገድ ጫካ ገብተው የነበሩ ወገኖች ተቀብለው ወደ ሰላማሚ ኑሯቸው እየተመለሱ ነው፡፡

"ኑ ሀገር እንስራ" ሲባል…

"ኑ ሀገር እንስራ" ማለት በሌላው ላይ ጣት ከመቀሰር ይልቅ የራሳችንን ድርሻ መወጣት ማለት ነው። ችግኝ መትከል፣ ግብር በታማኝነት መክፈል፣ ሕግን ማክበር፣ ዜጎች በተሰማሩበት የስራ መስክ ሁሉ ጥራት ያለው ሥራ መስራት፣ ሙስናን መቃወምና መታገል፣ እንደ የአንድ ሀገር ልጆች ልዩነቶቻችንን በሰላምና በውይይት መፍታት እና ለሌሎች መትረፍ ሁሉም የሀገር ግንባታ አካላት ናቸው።

ምክንያቱም ሀገር የምትገነባው በመንግሥት ብቻ አይደለም። አርሶ አደሩ በማሳ፣ መምህሩ በክፍል፣ ሐኪሙ በሆስፒታል፣ ኢንጂነሩ በግንባታ፣ ነጋዴው በታማኝነት፣ ወጣቱ በፈጠራ እና እናቶች በትውልድ ቀረጻ ጭምር ነው። እያንዳንዱ ዜጋ "እኔ ለኢትዮጵያ ምን አበርክቻለሁ?"ብሎ ራሱን ሲጠይቅ የሀገር ግንባታ በእውነት ይጀምራል።

ልማት የሚጀምረው በአእምሮ ነው። የበለጸገች ሀገር የምትገነባውም በተባበሩ ዜጎች ክንድ ነው፡፡ ስለሆነም ልዩነቶቻችንን እንደ ጥንካሬ በመቀበል፣ በመከባበር፣ በመተባበር እና በታማኝነት በመስራት የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት እንችላለን።

አዎን! ሀገር የምትገነባው በዜጎቿ ፅኑ እምነት፣ በትብብር፣ በትጋት እና በጋራ ራዕይ ነው። የኢትዮጵያ ነገ በዛሬው ውሳኔያችን፣ በዛሬው ሥራችን እና በዛሬው አንድነታችን ይወሰናል። ስንተባበር ልዩነታችን ጥንካሬ ይሆናል፤ ስንተማመን ተስፋችን ይጎለብታል፤ ስንሠራ ደግሞ ልማታችን ይፋጠናል።

ስለዚህ ዛሬ ከቃላት ወደ ተግባር፣ ከተስፋ ወደ ሥራ፣ ከመጠባበቅ ወደ ኃላፊነት እንሻገር። እጃችንን እናጣምር፣ ልባችንን እናቀራርብ፣ ለልጆቻችን የምንኮራባት ኢትዮጵያን በጋራ እንገንባ። በአንድ ድምፅ፣ በአንድ አላማ፣ በአንድ ቁርጠኝነት እንበል- ኑ ሀገር እንስራ!

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.