Logo
FBC
በመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋ በአንድ ነጥብ የተሰናበተችው ኩራሳኦ …

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ የተሳተፈችው ሀገር ኩራሳኦ በአንድ ነጥብ እና በስምንት የግብ ዕዳ የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን አጠናቅቃ ወደ ሀገሯ ተመልሳለች፡፡

በዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ሀገር ኩራሳኦ በዓለም ዋንጫ መድረክ የራሷን ታሪክ ፅፋ ከውድድሩ ተሸኝታለች፡፡

ኩራሳኦ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ በአራት ጊዜ የመድረኩ ሻምፒዮን ሀገር ጀርመን 7 ግብ ቢቆጠርባትም አንድ ግብ አስቆጥራ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በጨዋታው በርካታ ግብ ብታስተናግድም በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎዋ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡

በጀርመን ከደረሰባት የ7 ለ 1 ሽንፈት በኋላ በሁለተኛ የምድብ ጨዋታ ኢኳዶርን የገጠመቸው ኩራሳኦ 0 ለ 0 በመለያየት በመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋ አንድ ነጥብ ማሳካቷ ይታወሳል፡፡

ኩራሳኦ ከኢኳዶር በነበራት የምድብ 2ኛ ጨዋታ የ37 አመቱ ግብ ጠባቂ ሩም አስደናቂ ብቃት በማሳየት 15 ያለቀላቸው ኳሶችን በማዳን በደሴቲቱ ሀገር ትዝታ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የማይፋቅ ታሪክ ጽፏል፡፡

ግብ ጠባቂው በካንሳስ ሲቲ ስታዲየም በ68 ሺህ 98 ደጋፊዎች ፊት ስሙን በዓለም ዋንጫ ታሪክ በእግር ኳስ ትልቁ መድረክ ላይ በአጠቃላይ 27 ሙከራዎችን በማዳን የኢኳዶር ተጫዋቾች ግብ ሳያስቆጥሩ እንዲወጡ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

ግብ ጠባቂው ድንቅ እንቅስቀሴ ማሳየቱን ተከትሎ በወቅቱ በስፖርት ቤተሰብ አድናቆት እንደተቸረገው ይታወሳል፡፡

ኩራሳኦ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዋን ከኮትዲቯር ጋር አድርጋ 2 ለ 0 ተሸንፋ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን አጠናቅቃለች፡፡

ኩራሳኦ በዓለም ዋንጫ ካደረገቻቸው ሦስት የምድብ ጨዋታዎች ሁለቱን ተሸንፋ በአንዱ አቻ ተለያይታ 9 ግቦች ተቆጥረውባት አንድ ግብ ብቻ አስቆጥራለች፡፡

በዓለም ዋንጫ በመሳተፍ ትንሿ ሀገር በመሆን በቀዳሚነት የተቀመጠችው ኩራሳኦ በአንድ ነጥብ እና በስምንት የግብ ዕዳ የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን ጨርሳለች፡፡

በዓለም ዋንጫ በመሳተፍ ትንሿ ሀገር በመሆን አዲስ ታሪክ የጻፈችው ኩራሳኦ በድጋሚ በዓለም ዋንጫ መድረክ ትገኝ ይሆን የሚለው ይጠበቃል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.