Logo
EBC
የእንግሊዝ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ
*********************

የእንግሊዝ ባለሃብቶችና የንግዱ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ሀገራችን በሯ ክፍት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በለንደን በተካሄደው የዩኬ-ኢትዮጵያ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ያላት ተሳትፎ በቀጣናዊና በአኅጉራዊ ንግድ ያላትን ሚና እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላት ስትራቴጂያዊ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ በትራንስፖርት፣ በሎጂስቲክስ፣ በኃይል ትስስር እና በንግድ ላይ እያደጉ ከመጡ ኢንቨስትመንቶች ጋር ተዳምሮ፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት ቀጣናዊ ማዕከል ለመሆን የምታደርገውን ጉዞም ያጠናክረዋል ነው ያሉት።

ከእንግሊዝ፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ዓለም አቀፍ ባለሃብቶች ጋር ያለንን አጋርነት እናከብራለን ያሉት ሚኒስትሩ፣ እንደ ‘ብሪቲሽ ኢንተርናሽናል ኢንቨስትመንት' ያሉ ተቋማት በቴሌኮሙኒኬሽን፣ በፋይናንስ አገልግሎት፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በሎጂስቲክስ ዘርፎች ኢንቨስት በማድረግ በኢትዮጵያ ያላቸውን እምነት አሳይተዋል ብለዋል።

ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል የቆየውን ሁለንተናዊ መልካም ግንኙነት የሁለቱንም ወገኖች የጋራ ተጠቃሚነት ይበልጥ ወደሚያረጋግጥ አጋርነት ለማሸጋገር እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ ኢኮኖሚዎች አንዱ መሆኑን አንስተው፣ የእንግሊዝ ኩባንያዎች ወደ ሀገራችን በስፋት እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና ለዘላቂ ልማት ያላት ቁርጠኝነት የኢኮኖሚ ራዕይዋ ማዕከል ሆኖ መቀጡንም አብራርተዋል።

በአድማሱ አራጋው
#ethiopia #ebc #investment #uk_ethiopiaforum

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.