Logo
FBC
ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ተሞክሮ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እና ተቀባይነት ከማግኘት ባለፈ በተለያዩ ሀገራት ዘንድ እንደተሞክሮ እየተወሰደ ይገኛል፡፡

ለአካባቢ ጥበቃና ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ለመስጠት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2011 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ካስጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን 48 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ለተከታታይ ሰባት ዓመታት የተካሄደው መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን እና የኢኮኖሚ እድገትን ከማረጋገጥ ባለፈ የደን ሽፋንን በመጨመር ለአየር ንብረት ለውጥ ተጨባጭ መፍትሔ ሰጥቷል፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም የኢኮኖሚ ትስስሩን የበለጠ ያጠናከረ ሲሆን÷ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እንደ የዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) በመሳሰሉ ተቋማት እውቅና ያገኘ ሲሆን÷ በሀገራት ዘንድ ደግሞ እንደ መልካም ተሞክሮ እየተወሰደ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ መርሐ ግብሩን ባስጀመረች ማግስት ለጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ እና ሱዳን ችግኞችን በመላክ የአካባቢ ጥበቃ ጥረቷን ድንበር ተሻጋሪ ማድረግ ችላለች፡፡

በተመሳሳይ ፓኪስታን ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ ስትራቴጂያዊ አጋር በማድረግ በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ልምድ ለመውሰድ ስምምነት አድርጋለች፡፡

ይህንን ተከትሎም ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ውጤት ያመጣውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በማስፋፋት ለአረንጓዴ ዲፕሎማሲ የሰጠችው ትኩረት ውጤት እያመጣ ይገኛል።

ይህ ውጤት ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ መድረክ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ግንባር ቀደም ተዋናይ እንድትሆን አስችሏታል።

ዘንድሮም የተያዘውን የ8 ቢሊየን ችግኞች የመትከል ግብ ለማሳካት በሚደረገው ብሔራዊ የንቅናቄ ላይ ኢትዮጵያውያን ለተግባራዊነቱ እንዲረባረቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

በሚኪያስ አየለ

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.