Logo
EBC
የክረምት ደጋግ እጆች፦ የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ዋስትና አዲስ ምዕራፍ
********************

ክረምት በኢትዮጵያ፣ ምድር አረንጓዴ የምትለብስበትና ተፈጥሮ ራሷን የምታድስበት የተስፋ ማብሰሪያ ወቅት ነው።

ነገር ግን ይህ የዝናብ እና የብርድ ወቅት መጠለያ ለሌላቸው እና አቅመ ደካማ ለሆኑ ወገኖቻችን ከባድ ፈተናን ይዞ መምጣቱ አይቀሬ ነው።

ሆኖም ኢትዮጵያውያን ይህን ተፈጥሯዊ ፈተና በትብብር እና በመደጋገፍ የማለፍ የቆየ እና የዳበረ ታላቅ ባህል አላቸው።

ዘር ለሌለው ዘር በመስጠት፣ መጠለያ ለሌለው መጠለያ በመሥራት እና አቅም ላነሳቸው ደቦ በመውጣት ነው ይህን ከባድ ጊዜ በጋራ የሚሻገሩት።

በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ታሪክ ውስጥ በራስ ተነሳሽነት እና በጋራ ትብብር ላይ የተመሠረቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ጥልቅ ሥር ያላቸው የባህል እሴቶቻችን ናቸው።

ይህ በችግር እና በፈተና ወቅት እርስ በርስ የመረዳዳት ሥነ ልቦናዊ ዝግጁነት፣ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተቋማዊ እና ስትራቴጂያዊ ሀገራዊ ንቅናቄ ተሸጋግሯል።

አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በ2010 ዓ.ም የነበረው የ10.8 ሚሊዮን ወጣቶች ተሳትፎ በ2017 ዓ.ም ወደ 25 ሚሊዮን አድጓል።

በተመሳሳይ መልኩ፣ በመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች ቁጥር ከ13.6 ሚሊዮን ወደ 53 ሚሊዮን ከፍ ብሏል።

በ2015 ዓ.ም ብቻ በተካሄደው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ21.5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በመሰማራት ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት አገልግሎት ማበርከታቸው የንቅናቄውን ግዙፍ ሀገራዊ ፋይዳ በተግባር ያረጋግጣል።

ይህ ታላቅ ጥረት አብዛኛው ሕዝብ ከተለመደው የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን ውጭ በሆነበት ሁኔታ ላይ ክፍተቱን ለመሙላት የሚያስችል አማራጭ እና ውጤታማ ማኅበራዊ ዋስትና ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

የዘመቻው ዋነኛው ስኬት፣ አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ረገድ የመጣው ስር ነቀል ለውጥ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የክረምት ወቅት ከመግባቱ በፊት የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ዓመታዊ መርሐ ግብር ማስተዋወቃቸው ይታወሳል።

ይህ መርሐ ግብር ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ46 ሺህ በላይ ቤቶችን በአዲስ መልክ በመገንባት ዜጎችን በዝናብ እና በብርድ ከመሰቃየት ታድጓቸዋል።

የታሪካዊው የአዋሬ መንደር ስር ነቀል ለውጥ ለዚህ ታላቅ ማሳያ ነው። ቀደም ሲል ለኑሮ እጅግ አስቸጋሪ የነበሩ ያረጁ የጭቃ ቤቶች ዛሬ በአዲስ መልክ ተገንብተው ጽዱ፣ ምቹ እና ለሰው ልጅ ክብር የሚመጥኑ ሆነዋል።

የዘንድሮው የ2018 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር ደግሞ የከተማ ልማትን ከገጠር ልማት ጋር ለማስተሳሰር የሚያስችል አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ከፍቷል።

ይህ እሳቤ አርሶ አደሩ ያሉትን አካባቢያዊ ጸጋዎች ተጠቅሞ፣ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ቁርኝት በማጠናከር ዘመናዊ እና ጽዱ አኗኗር መምራት እንዲችል ለማድረግ ያለመ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር ሲያስጀምሩ ያስተላለፉት ጥሪ የንቅናቄውን መንፈስ በጉልህ ያሳያል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የክረምቱ ወቅት ሲደርስ፣ እኛም ለወገኖቻችን የምንዘረጋው የደግነት እጅ አብሮ ይጀግናል!" በማለት ነው መልዕክታቸውን የጀመሩት።

አክለውም፣ "ሀገራችንን በጋራ ማንሳት የምንችለው፣ አንዳችን ለሌላችን እጃችንን ስንዘረጋ ብቻ ነው! ስለሆነም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዚህ ሥራ እንዲሳተፍ ጥሪዬን አቀርባለሁ” በማለት ሁሉም በሚችለው መንገድ ለመርሐ ግብሩ መሳካት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

እኛስ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ አሻራችንን ለማሳረፍ ምን ያህል ተዘጋጅተናል? የክረምቱን ቅዝቃዜ በደግነት እጆቻችን እናሙቀው!

በለሚ ታደሰ
#voluntarism #socialsecurity #communityservice #transformingethiopia

13 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.