Logo
EBC
ከአፈር ጥበቃ እስከ ምርታማነት - የአረንጓዴ ዐሻራ ትሩፋት በካፋ ዞን
*********************************

ኢትዮጵያ ለተከታታይ ዓመታት እየተገበረችው የምትገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ የበርካታ አርሶ አደሮችን የኑሮ ዘይቤ ከመቀየር ባለፈ ለምርታማነት ዕድገት መሠረት እየሆነ ይገኛል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል፣ በካፋ ዞን የጊምቦ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ለኢቢሲ እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት ያከናወኑት የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

ይህም የአካባቢው አየር ንብረት ተጠብቆ እንዲቆይና የሰብል ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል። አርሶ አደሮቹ ከጥንት ጀምሮ የነበራቸውን ደንን የመጠበቅና የመንከባከብ ባህል በአረንጓዴ ዓሻራ መርሐ ግብር ይበልጥ በማጠናከር፣ ለዘላቂ ተጠቃሚነታቸው በትጋት እየሠሩ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

የካፋ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ እና ኅብረት ሥራ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ገረመው ገብሬ በበኩላቸው፣ በመርሐ ግብሩ የተከናወኑ ተግባራት ለዞኑ ምርታማነት ዕድገት አይነተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ለምግብነት የሚውሉና ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ፣ አሁን ላይ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የሞክትል እና የተፈጥሮ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ውብሸት ዘነበ በበኩላቸው፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በክልሉ 330 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ባላቸው ችግኞች መሸፈኑን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ሀብቶችን በተገቢው ሁኔታ እንዲንከባከብና በሂደቱም ተጠቃሚ እንዲሆን የተከናወኑ ሥራዎች ስኬታማ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ውብሸት፤ በክልሉ የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት ምጣኔም ከ88 በመቶ በላይ መድረሱ እንደተረጋገጠ አስታውቀዋል።

በሰለሞን ባረና
#ethiopianbroadcastingcorporation #ethiopia #green #legacy

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.