Logo
EBC
ከአሸዋ ማዕበል ወደ አረንጓዴ ሀብት፦ በረሃዎችን ወደ ቱሪዝም መዳረሻነት የቀየረው የቻይና የአረንጓዴ ልማት ተሞክሮ
****************

ቻይና ዛሬ በዓለም ላይ የታላላቅ የደን ማገገሚያ እና የበረሃማነት መከላከል ፕሮጀክቶች ባለቤት ከሆኑ ሀገራት መካከል ትጠቀሳለች።

የዛሬው ስኬቷ ታዲያ ከአሸዋ ማዕበል፣ ከውሃ እጥረት እና ከበረሃ መስፋፋት ጋር ከተደረገ የረጅም ጊዜ ትግል በኋላ የተገኘ ነው።

በተለይ በጎቢ እና በኩቡቺ አካባቢዎች የነበረው ሰፊ በረሃማ መሬት ለዓመታት የአካባቢው ነዋሪዎችን ሕይወት አስቸጋሪ አድርጎት ቆይቷል።

በእነዚህ አካባቢዎች በየጊዜው የሚነሳ ኃይለኛ የአሸዋ ማዕበል ከተሞችን ይመታ ነበር፤ የእርሻ መሬቶችም በአሸዋ ይሸፈኑ ነበር።

ይህን ችግር ለመፍታት ቻይና በሚሊዮን ሄክታሮች በሚለካ መሬት ላይ ዛፎችን፣ ሳሮችን እና በደረቅ አካባቢ የሚበቅሉ ችግኞችን ተከለች።

የአሸዋ ክምችቶች እንዳይንቀሳቀሱ ልዩ የሆኑ የሣር አጥር ቴክኒኮችን በመጠቀም እና የውሃ ማቆያ ሥርዓቶችን በመገንባት አስደናቂ ውጤት ማስመዝገብ ቻለች።

በአንድ ወቅት ሕይወት ይኖርባቸዋል ተብለው የማይታሰቡ የነበሩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዛሬ በአረንጓዴ እጽዋት ተሸፍነዋል።

የዱር እንስሳት ተመልሰዋል፤ የአየር ጥራት ተሻሽሏል፤ የአካባቢው ሰዎችም ከእርሻ፣ ከደን ውጤቶች እና ከቱሪዝም ልማት ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ጀምረዋል።

በአሸዋ ተራሮች ላይ ለመዝናናት፣ አረንጓዴ ፓርኮችን ለመጎብኘት፣ የኢኮ-ቱሪዝም ተሞክሮዎችን ለመቅሰም እና በአካባቢው የተፈጠረውን አስደናቂ ለውጥ ለማየት ጎብኚዎች በሚሊዮኖች ወደነዚህ አካባቢዎች ይተማሉ።

በተለይ ኩቡቺ በረሃ የአካባቢ ጥበቃ እና የኢኮ-ቱሪዝም ስኬት ተምሳሌት ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይጠቀሳል። ይህ ተሞክሮ ለሌሎች ሀገራት ጭምር ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው።

ዛሬ ለዛፍ ተከላ የሚወጣ ወጪ ነገ በአካባቢ ጥበቃ፣ በግብርና፣ በቱሪዝም እና በኢኮኖሚ ዕድገት በብዙ እጥፍ የሚመለስ ኢንቨስትመንት መሆኑን ያመላክታል።

ኢትዮጵያም በአረንጓዴ ዐሻራ ያመጣችውን ለውጥ አጠናክራ ከቀጠለች፣ ዛሬ የሚተከለው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ችግኝ ነገ ለትውልድ የሚተርፍ የደን ሀብት፣ የውሃ ምንጭ፣ የካርቦን ማቆያ እና አዳዲስ የኢኮ-ቱሪዝም መዳረሻ ይሆናል።

ዛሬ የምንተክለው ችግኝ የነገ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የቱሪዝም ገቢ እና የአረንጓዴ ኢትዮጵያ መሠረት ነው።

በሀብተሚካኤል ክፍሉ
#greenlegacy #chinagreenwall #ecotourism #climateaction #environmentalrestoration #ebc

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.