Logo
FastMereja
14ኛው ሀገራዊ እና የመጀመሪያው የምስራቅ አፍሪካ የአንቲማይክሮቢያል ግንዛቤ ቀን ተከበረ!
#fastmereja : የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች መላመድ ወይም መቋቋም (AMR) እያደረሰ ያለው ዘርፈ-ብዙ ጉዳት በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሰው፣ በእንስሳትና በአካባቢ ጤና እንዲሁም በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑ ተገለፀ።

ይህ የተገለጸው በአገር አቀፍ ደረጃ ለ14ኛ ጊዜ፣ በምስራቅ አፍሪካ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረውን ብሔራዊ የአንቲማይክሮቢያል ግንዛቤ ቀንን አስመልክቶ በተዘጋጀው ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረክ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ750 ሺህ በላይ ሰዎች በዚህ ችግር ሳቢያ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የተገለፀ ሲሆን አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ ግን እ.ኤ.አ በ2050 የሟቾች ቁጥር ወደ 10 ሚሊዮን ሊጠጋ እንደሚችልና በዓለም ኢኮኖሚ ላይም እስከ 10 ትሪሊዮን ዶላር (ከ2% እስከ 3%) ኪሳራ ሊያደርስ እንደሚችል እና ይህ የኢኮኖሚ ኪሳራ በተለይ በታዳጊ አገራት ላይ ከ5% በላይ ሊበልጥ እንደሚችል ተነግሯል።

በኢትዮጵያ አሁንም ተላላፊ በሽታዎች ከፍተኛውን ቁጥር ይዘው እንደሚገኙ የተገለፀ ሲሆን፣ ጀርሞች መድኃኒቶችን የመቋቋም አቅም እንዲያዳብሩ የሚያደርጉ ዋና ዋና መንስኤዎች የታዘዘን መድኃኒት ሳይጨርሱ ማቋረጥ፣የመውሰጃ ሰዓትን ማዛባት፣ያለሀኪም ትዕዛዝ መድኃኒት ገዝቶ መውሰድ፣እና የሌላ ሰውን መድኃኒት "ያድናል" በሚል እሳቤ መውሰድ ዋነኞቹ መሆናቸው ተጠቅሷል።

ይህ አሠራር በበሽታዎች የመዳን ዕድልን ከመቀነሱም በላይ የሆስፒታል ቆይታንና የሕክምና ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረው እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ይህንን ችግር ለመከላከል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት "ሀገር አቀፍ የማህበረሰብ ፋርማሲ አስገዳጅ ደረጃ መመሪያ" ያወጣ ሲሆን፣ የአምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅዱን ባለፈው ግንቦት 2026 ዓ.ም ከወጣው የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የ10 ዓመት የAMR መከላከያ ዕቅድ ጋር የማስማማት ሥራ መሠራቱ ተረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ፋርማሲስቶች ማኅበር (EPA) ከዩኬ የጤና ደኅንነት ኤጀንሲ (UKHSA)፣ ከዓለም አቀፍ የፋርማሲዩቲካል ፌዴሬሽን (FIP)፣ ከአፍሪካ ፋርማሲዩቲካል ፎረምና ከዩኒዶ (UNIDO) ጋር በመሆን የ"አንድ ጤና" (One Health) አካሄድን ለማጠናከር እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ችግሩን ለመከላከል መላው ማኅበረሰብ፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና በተለይም ሕዝብ ዘንድ የመድረስ ከፍተኛ አቅም ያላቸው መገናኛ ብዙኃን (ሚዲያዎች) የተቀናጀ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.