Logo
FBC
የዓለም ዋንጫ ትዝታዎች...

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከጅማሮው ከኳስ ውበቱ ይልቅ ከጀርባው ያለው ፖለቲካ አይሎ ከመታየቱ ባለፈ በርካታ ውዝግቦችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ውስጥ ስማቸው ጎልቶ ከሚነሳና የብዙሃንን ቀልብ መሳብ ከቻሉ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ነው ጋዜጠኛ ማርቆስ ኤልያስ።

በተለያዩ ታዋቂ ጋዜጦች የስፖርት ዓምድ ላይ ለበርካታ ዓመታት በመጻፍ የዳበረ ልምድ አካብቷል፡፡ ጋዜጠኛ ማርቆስ በሬዲዮ ሞገድም በሚያቀርባቸው ተወዳጅ ስፖርታዊ ዝግጅቶቹ የብዙዎችን ልብ ማሸነፍ ችሏል።

ማርቆስ በተለያዩ መድረኮች ላይ በሚያቀርባቸው ጥልቅ የስፖርት ትንታኔዎች በአድማጭና ተመልካች ዘንድ እጅግ የተወደደ ነው፡፡ በተለይም ያለፉ ክስተቶችን፣ ስታቲስቲክሶችን እና ታሪኮችን በቅጽበት አስታውሶ የመተንተን ልዩ ብቃቱ መለያው ነው።

መተሃራ አካባቢ ተወልዶ ያደገው ማርቆስ፤ የእግር ኳስ ፍቅር ልቡን የገዛው ገና በልጅነቱ ነበር። በወቅቱ ትልቅ ሕልሙ ጎበዝ የእግር ኳስ ተጫዋች መሆን የነበረ ቢሆንም፣ለትምህርት ቅድሚያ በመስጠቱ የእግር ኳስ ህልሙን ሳያሳካ እንደቀረ ያስታውሳል፡፡

ሆኖም ግን የስፖርት ጋዜጠኛው ማርቆስ መጫወት ባይችልም ኳስን በጥልቅ ከመውደዱ የተነሳ ዛሬም የስፖርቱ ዓለም የዕለት ተዕለት ሕይወቱና የሙያ እንጀራው ሆኖ ቀጥሏል።

ሁልጊዜም ቢሆን "የሀገር ውስጥ ስፖርትን ማሳደግ" የዘወትር ትልቅ ምኞቱና የሥራው ዋና ግብ መሆኑን በኩራት ይናገራል።

ዛሬ በጉጉት የሚጠበቀው የዓለም ዋንጫ ውድድር በይፋ የሚጀመርበት ዕለት በመሆኑም ጋዜጠኛው ስለ ውድድሩ ያለፉ ታሪኮች እና ወቅታዊ ሁኔታዎችን በማስመልከት ሰፊ ትንታኔ ሰጥቷል።

ያለፉትን የዓለም ዋንጫ ታሪኮች ሳያሰለች እና ትውስታዎችን እያጣቀሰ የሚተነትነው ማርቆስ፤ ዛሬ ስለሚጀመረው ታላቅ መድረክ አንኳር ሃሳቦችን አንስቷል፡

የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከጅማሮው ከኳስ ውበቱ ይልቅ፣ ከጀርባው ያለው ፖለቲካ አይሎ የታየበትና በርካታ ውዝግቦችን እያስተናገደ ነው ይላል፡፡

ጋዜጠኛው ማርቆስ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት የነበሩትን የሀገራት ፍጥጫዎች፣ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዎችና ከሜዳ ውጭ ያሉትን ትኩሳት በዝርዝር በመዳሰስ በርካታ አዳዲስ ሃሳቦችንና እይታዎችን አጋርቶናል።

በቅድስት ዘውዱ

ጋዜጠኛ ማርቆስ ኤልያስ ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረገውን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ፦ https://youtu.be/BA7Rsnkzj...

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.