Logo
FBC
በ2014 ዓለም ዋንጫ የደመቀው ጀምስ ሮድሪጌዝ…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም ሕዝብ በጉጉት የሚጠብቀውና በየአራት ዓመቱ የሚደረገው ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ ዓለም ዋንጫ ሁሌም አዳዲስ ክስተቶችን እያስመለከተ ያልፋል፡፡

የዓለም ዋንጫ በመጣ ቁጥር አዳዲስ ኮከቦችን እና በመድረኩ ድንገት ልዩነት ፈጥረው የእግር ኳስ ቤተሰብን ቀልብ የሚስቡ ተጫዋቾችን መመልከት የተለመደ ነው፡፡

ከመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ ውድድር ጀምሮ እስከ ኳታሩ የዓለም ዋንጫ ድረስ የተለያዩ አስደናቂ ኮከቦች በመድረኩ መታየታቸው አይዘነጋም፡፡

በፈረንጆቹ 2014 ብራዚል ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ውድድር ደግሞ የመድረኩ ክስተት እና አስገራሚ ኮከብ ሆኖ ብቅ ያለው ኮሎምቢያዊው ተጫዋች ጀምስ ሮድሪጌዝ ነበር፡፡

በወቅቱ በመድረኩ ኮሎምቢያዊው የ22 ዓመቱ ተጫዋች ጀምስ ሮድሪጌዝ ሜዳ ላይ በሚያሳየው እንቅስቃሴ የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ችሏል፡፡

ብራዚል ባዘጋጀችው መድረክ ጀርመን ዋንጫውን ጀምስ ግን የሁሉንም ልብ ነበር ያሸነፈው፡፡

በወቅቱ ተስፋዎች ሁሉ ልማደኛው የግብ አዳኝ ራዳሜል ፋልካኦ ላይ ቢሆንም እሱ መጎዳቱን ተከትሎ ኮሎምቢያ ከምድብ ታልፋለች ብሎ የገመተ አልነበረም፡፡

ኮሎምቢያ ግን አንድ የሚያሻግራት እና እግሮቹ እጅግ አስፈሪ የ22 ዓመት ወጣት ኮከብ ድንገት አገኘች፡፡

ብራዚላዊያን በደገሱት የ2014 የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ እንደ ጀምስ ሮድሪጌዝ የነገሰ ተጫዋች ማግኘት ከባድ ነበር፡፡

የእርሱን ያህል ግቦችን ያስቆጠረ፣ የእርሱን ያህል ለብሔራዊ ቡድኑ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ፣ በአስደናቂ እንቅስቃሴ እና በውብ ግቦች ተመልካቾችን ያዝናና አልነበረም።

በመድረኩ ስድስት ግቦችን ያስቆጠረው ወጣቱ ተጫዋች ከስድስቱ በኡራጓይ መረብ ላይ ያረፈችው ግብ የኮሎምቢያ እና የጀምስ መታሰቢያ ብቻ ሳትሆን ዓለም ዋንጫ በመጣ ቁጥር ከምርጦቹ አንዷ ሆና ተመዝግባለች፡፡

ጀምስ ሮድሪጌዝ ኡራጓይ ላይ ባስቆጠራት አስደናቂ ግብ ምርጥ ግብ በመባል የፑሽካሽ ሽልማትን አሸንፏል፡፡

ጀምስ ለኮሎምቢያ ባደረጋቸው እያንዳንዱ ጨዋታዎች ምርጥ ብቃቱን በማሳየት ሀገሩን ለሩብ ፍጻሜ አብቅቷል፡፡

ጀምስ ሮድሪጌዝ በዓለም ዋንጫው ስድስት ግቦችን በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን የውድድሩን የወርቅ ጫማ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

ከዓለም ዋንጫው ጎን ለጎን ገና ከውድድሩ ሳይመለስ እርሱን ለማስፈረም በርካታ ታላላቅ ክለቦች ፍላጎት ማሳየታቸው አይዘነጋም፡፡

የስፔኑ ኃያል ክለብ ሪያል ማድሪድ ይህንን የኮሎምቢያ ወጣት እና በዓለም ዋንጫው የተለያዩ ሀገራት ደጋፊዎች ልብ ውስጥ የቀረውን ጥበበኛ ማስፈረሙ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ ዓለም ላይ ያሉ በርካታ ክለቦች እሱን ለማስፈረም ቢፈልጉም ሪያል ማድሪድ የግሉ አደረገው፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ ከዓለም ዋንጫው በብራዚል ተሸንፎ ሲሰናበት የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ወደ ጀምስ በማቅናት አጽናንተውታል፡፡

ትልቅ ደረጃ ይደርሳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ጀምስ ሮድሪጌዝ እንደተጠበቀው ሳይሆን መቅረቱ ይታወቃል፡፡

በወንድማኝ ጸጋዬ

8 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.