Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ስፖርት) ቀያይ ሰይጣኖቹ ለፕሪሚየር ሊጉ ባስገቡት የዘንድሮ የተጫዋቾች ዝርዝር መሰረት በኦልድ ትራፎርድ ግርማ ሞገስ ነበራቸው የተባሉ ተጫዋቾች የማንቸስተር ቆይታቸው ማብቃቱ በይፋ ተረጋግጧል። ከነዚህም መካከል ዋነኛው እንግሊዛዊው የክንፍ ተጫዋች ጃዶን ሳንቾ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ ከ73 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ካዝናውን አራቁቶ ያመጣው ይህ ኮከብ፣ ከክለቡ ጋር የነበረው ቆይታ እጅግ አሳዛኝ እና ኪሳራ የበዛበት ሆኖ አልፏል። አቋሙን ማግኘት ተስኖት ከቀድሞ አሰልጣኞች ጋር ጭምር እሰጥ አገባ ውስጥ ገብቶ የነበረው ሳንቾ.. በመጨረሻም የክለቡን በር ለዘለቄታው ዘግቶ ወጥቷል። ከእሱ ጋርም ብራዚላዊው አንጋፋ አማካይ ካሴሚሮ እና ታይረል ማላሲያ ስንብታቸው ተረጋግጧል።

ማንቸስተር ዩናይትድ ባወጣው ይፋዊ የመሰናበቻ መግለጫ "ጃዶን ሳንቾ በ2021 ወደ ኦልድ ትራፎርድ ከመጣ በኋላ የ2023ቱን የካራባኦ ካፕ ካነሳው ስብስብ አንዱ ነበር። ወደ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በውሰት ከመመለሱ፣ እንዲሁም በቼልሲ እና አስቶን ቪላ ጊዜያዊ ቆይታዎችን ከማድረጉ በፊት ለክለቡ 83 ጨዋታዎችን አድርጓል። ክለባችን ካሴሚሮ፣ ታይረል እና ጃዶን ላበረከቱት አስተዋጽኦ እያመሰገነ፣ ለቀጣይ የእግር ኳስ ህይወታቸው መልካሙን ሁሉ ይመኛል" ብሏል።

የማንቸስተር ዩናይትድ ማልያ ከብዶት የታየው የ26 ዓመቱ አጥቂ፣ በአምስት ዓመት የዩናይትድ ቆይታው በሁሉም ውድድሮች ማግባት የቻለው 12 ጎሎችን እና 6 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ማቀበል ብቻ ነው። ይህ ደካማ አቋሙ የቀድሞ የክለቡን ተጫዋቾች ሳይቀር አበሳጭቷል። በተለይም ሉዊስ ሳሃ፣ ሳንቾን "በማንቸስተር ዩናይትድ ታሪክ እጅግ አሳዛኙ ፈራሚ" ሲል ከባድ ትችት ሰንዝሮበታል።

ሳሃ በቁጭት ስሜት ሲናገር... "ከመምጣቱ በፊት በቦሩሲያ ዶርትሙንድ ያሳየው አስገራሚ ብቃት እና የነበረው ተሰጥኦ ታላቅ ተስፋ ሰጥቶን ነበር፤ እንግሊዝ መጥቶ ያ ሁሉ መጥፋቱ ግን እንቆቅልሽ ሆኖብኛል። እኔ እግር ኳስ ተጫዋች በመሆኔ እድለኛ ነበርኩ፣ ግን በጉዳት ብዙ ጊዜ አሳልፌያለሁ። በእሱ ዕድሜ እና ተሰጥኦ የሱን ያህል ጨዋታዎችን መጫወት ብችል ምንኛ መታደል ነበር... አስገራሚ ነገሮችን ማድረግ የሚችል ልጅ ነው፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ ችሎታው እና የተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ሲባክኑ ማየት በእጅጉ ያሳዝናል" ብሏል።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቢቸገርም በጀርመን ምድር ግን ሳንቾ አሁንም ትልቅ ከበሬታ እና ስም አለው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ፣ ተጫዋቹ ከ2021 ጀምሮ የጠፋበትን የእግር ኳስ ህይወቱን ዳግም ለማንሰራራት ለሶስተኛ ጊዜ ወደ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ለማምራት በሩን ክፍት አድርጓል። የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ኒኮ ኮቫችም ለዚህ ዝውውር አረንጓዴ መብራት አብርተዋል እየተባለ ይገኛል።

ሳንቾ የህይወቱን ምርጥ ጊዜ ያሳለፈው በዚሁ በሲግናል ኢዱና ፓርክ ሲሆን.. በመጀመሪያ ቆይታው በ137 ጨዋታዎች በ114 ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበረው። በ2024 በውሰት ተመልሶ ክለቡን እስከ ዌምብሌዩ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ማድረሱም አይዘነጋም። ወደ ቡንደስሊጋው መመለሱ፣ ከ2021 ጀምሮ ለተለየው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ዳግም እንዲጠራ የሚያስችለውን መተማመን ሊሰጠው ይችላል።

የፋይናንስ መዛግብቱን ለማስተካከል እና አዲስ ጠንካራ ስብስብ ለመገንባት ቆርጦ የተነሳው ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋዮቹን እያጸዳ ይገኛል። ከሳንቾ በተጨማሪ አንጋፋው ብራዚላዊ አማካይ ካሴሚሮ እና የግራ መስመር ተከላካዩ ታይረል ማላሲያ በኮንትራት መጠናቀቅ ምክንያት ተሰናብተዋል። ከሪያል ማድሪድ መጥቶ በአራት የውድድር ዘመናት ቆይታው የካራባኦ ካፕ እና የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫዎችን ያነሳው ካሴሚሮ፤ እንዲሁም ከ2022 የፌይኖርድ ዝውውሩ በኋላ በጉዳት እየታመሰ 50 ጨዋታዎችን ብቻ ማድረግ የቻለው ማላሲያ የክለቡን በር ዘግተው ወጥተዋል።

አዲሱ የማንቸስተር ዩናይትድ የስፖርት አመራር እነዚህን ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋይ ተጫዋቾች ማሰናበቱ፣ በቀጣዩ የዝውውር መስኮት አዳዲስ እና ወጣት ደም ለማስገባት በደመወዝ በጀቱ ላይ ሰፊ የፋይናንስ ነጻነትን ፈጥሮለታል። አሁን የሁሉም አይን ዩናይትድ ይህንን ክፍተት በማን እንደሚተካው ላይ አርፏል!

4 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.