Logo
Getu Temesgen
የፋይዳ መታወቂያና የዲያስፖራ ሂሳብ እግድ፡
እግዱን የምታነሱበት 4 መንገዶች!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመሪያ መሠረት በዋና ዋና ከተሞች በሚገኙ የባንካችን ቅርንጫፎች የተከፈቱ የባንክ ሂሳቦች ባለቤቶች የሆኑና እስከ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም ከፋይዳ መታወቂያ ጋር ሳያጣምሩ የቀሩ ደንበኞች በቀጣይ እስኪያጣምሩ ሂሳባቸው በጊዜያዊነት እንዳይንቀሳቀስ መደረጉ ይታወቃል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መኖሪያቸውን ከኢትዮጵያ ውጭ ያደረጉ ደንበኞች የባንክ ሂሳባቸውን ከፋይዳ መታወቂያ ጋር ማጣመር ሳያስፈልጋቸው በጊዜያዊነት በልዩ ሁኔታ መስተናገድ የሚችሉበትን አሠራር ዘርግቷል።

በዚህ መሠረት ከዚህ በፊት ሂሳብ በሚከፍቱበት ወቅት የመኖሪያ አድራሻቸው ከኢትዮጵያ ውጭ እንደሆነ በባንካችን የመረጃ ቋት የተመዘገበ ማስረጃ ያቀረቡ ደንበኞች ሂሳብ ያልታገደ መሆኑን እያሳወቅን፤ በተለያየ ምክንያት ውጭ ሀገር እንደሚኖሩ በባንካችን የመረጃ ቋት ላይ ያላስመዘገቡ እና የባንክ ሂሳባቸው የታገደባቸው ደንበኞች ከዚህ በታች በተገለፀው አግባብ መስተናገድ የሚችሉ መሆኑን እንገልፃለን፡

1. ከኢትዮጵያ ውጭ መኖራቸውን የሚገልፅ ማስረጃ ለምሳሌ - የትምህርት ማስረጃ፣ የህክምና ማስረጃ፣ የውጭ ሀገር መንጃ ፈቃድ፣ ከውጭ ሀገር የተሰጠ ውክልና፣ የመኖሪያ ፈቃድ (የሎው ካርድ)፣ የሥራ ፈቃድ ወይም ሀገር ውስጥ እያሉ የተሰጠ ውክልና ሆኖ ነገር ግን ውክልናው ላይ ውጭ ሀገር መኖራቸውን የሚገልፅ ሀሳብ ካለ በህጋዊ መኪሎቻቸው አማካኝነት በማቅረብ እግዱን ማስለቀቅ ይችላሉ፤

2. ዲፕሎማቶች የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ መታወቂያቸውን በማሳየት ወይም ሂሳቡ የተከፈተው በዲፕሎማት መታወቂያ ከሆነ እግዱ ተነስቶላቸው ሂሳባቸውን ማንቀሳቀስ ይችላሉ፤

3. ደንበኛው በውጭ ሀገር እንደሚኖር የሚያረጋግጥ የኢሜይል መልእክት በኢምባሲ/ቆንስላ በኩል ከመጣ እግዱ በጊዜያዊነት ተነስቶላቸው መሰተናገድ ይችላሉ፤

4. በተጨማሪም ደንበኞች በውጭ ሀገር መኖራቸውን ሊያስረዱ የሚችሉ ማስረጃዎችን በቀጥታ የባንክ ሂሳቡ በተከፈተበት ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ የኢ-ሜል አድራሻ ወይም በዲያስፖራ ባንኪንግ ክፍል የኢ-ሜል አድራሻ DiasporaBankingcbe.com.et በመላክ እግዱን በጊዜያዊነት ማስነሳት ይችላሉ።

*
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ሁሌም የሚተማመኑበት ባንክ!

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.