Logo
EBC
የመደመር አንቀጽ

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ለሀገራችን እንደሚሆን አድርገን በፈጠራና በፍጥነት እየተገበርነው ነው። በለውጡ ዕሳቤ መሠረት ለችግሮቻችን የምንሰጠው መፍትሔ አምስት ማእቀፎች ያሉት ሲሆን፤ ለአየር ንብረት ለውጥ ችግር በዚሁ መርሕ መሠረት ምላሽ እየሰጠን እንገኛለን።

አንደኛው፥ ሥራው በመርሕ የሚመራ መሆኑ ነው። ያም ማለት ኢትዮጵያን እንደገና መልሶ በአረንጓዴ ልብስ የማልበስ መርሕ ነው። ጉዳዩ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የተያያዘ እና ብልጽግናችንን የሚወስን ነው።

ሁለተኛው፥ መርሐ ግብሩን በራሳችን ልንተገብረው የምንችል መሆን አለበት የሚለው ነው። ከውጭ ርዳታ፣ ፈንድ እና ትብብር ጋር ማገናኘት የለብንም። በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ዐቅም ሊተገበር የሚችል መሆን አለበት።

ሦስተኛው፥ ለኮሙኒኬሽን ወይም ለኮንፈረንስ ወይም ለሐሳዊ የአካባቢ ጥበቃ ዝና ማግኛ የሚሠራ መሆን የለበትም። የምንሠራው ሥራ በሀገራችን ላይ ተጨባጭ ውጤት የሚያመጣ መሆን አለበት የሚለው ነው። ለውጡም በአየር ንብረት ሚዛን፣ በምግብ፣ በአፈር ጥበቃ፣ በወንዞች ፍሰት መስተካከል፣ ወዘተ. መታየት አለበት።

አራተኛው፥ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በሚመለከታቸው ተቋማት ታቅዶ ቢመራም፤ ሕዝቡን በሙሉ ሊያሳትፍ መቻል አለበት የሚለው መርሕ ነው። ተሳትፎውም የተለያዩ ማኅበረሰቦችን፣ የማኅበረሰብ ክፍሎችን፣ የአድሜ ደረጃዎችን፣ የአምነት አካባቢዎችን፣ ጾታዎችን፣ ወዘተ. እንዲያካተት ተደርጎ መዘርጋት አለበት። ይህ ደግሞ አምስተኛውን መርሕ ለመተግበር ያስችላል።

አምስተኛው፥ የባህል ለውጥ ማምጣትን የሚመለከት ነው። ዛፎችን መትከል፣ መንከባከብና በተገቢው መንገድ መጠቀም የዘመቻ ሥራ ከመሆን አልፎ የሕዝብ ባህል እንዲሆን መሥራት ነው።

አረንጓዴ ዐሻራ በእነዚህ የመፍትሔ መንገዶቻችን የተመራ ነው። መርሑ፥ ኢትዮጵያን በሀገር በቀል ዛፎች መልሶ ማልበስ ነው። ይህንንም ራሳችን ችግኞችን በማፍላት፣ ሕዝብን በማስተባበርና ሀብትን በመቆጠብ ማከናወን ችለናል። የአረንጓዴ ዐሻራን አካባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ውጤት የምንለካባቸው መለኪያዎች አሉ። ለእነዚህ መለኪያዎች ታማኝ በመሆንም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ አያያዝ በመተግበርና የግምገማ ሥርዓት በማበጀት መርተነዋል።

የመደመር መንግሥት
ገጽ 186
Ethiopian Broadcasting Corporation #etv #ebcdotstream #medemer #ethiopia

8 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.