Logo
EBC
ምክር ቤቱ የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ እና የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጆችን ለየቋሚ ኮሚቴዎቹ መራ
**********************

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባው የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ እና የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ ወደሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

በምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ሁለቱንም ረቂቅ አዋጆች አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ግብርና ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለኢንዱስትሪ ልማትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ መሠረት በመሆኑ የአሠራር ሥርዓቱን በማላቅ ወደ ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪና የገበያ መር ሥርዓት ማሸጋገር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም አዋጁ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮችን በግብርና ቢዝነስ ኩባንያ በማደራጀትና በማቀናጀት ምርታማነትንና የምርት ጥራትን ለማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስፈን ወሳኝ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

ምክር ቤቱም በአባላቱ የተሰጡትን ሐሳብና አስተያየቶች ካዳመጠ በኋላ ረቂቅ አዋጁን ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መርቶታል።

በተመሳሳይ መልኩ ምክር ቤቱ የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መርቷል።

ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው ረቂቅ አዋጁ የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱን በማዘመን በታክስ ከፋዩ ዘንድ የሚነሱ መሠረታዊ የፍትሐዊነትና የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በሀገራችን የታክስ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ተጠያቂነትን፣ ቅልጥፍናን፣ ፍትሐዊነትንና ግልጽነትን ለማስፈን የታክስ ሕጎችን በተጠናከረ መልኩ ለማስፈጸም እንዲሁም በታክስ ከፋዩና ሰብሳቢው መካከል ያለውን ግንኙነት በሕግ የበላይነት ላይ እንዲመሠረት የሚያስችሉ ቁልፍ ድንጋጌዎችን የያዘ መሆኑን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱን ከዘመናዊና ዓለም አቀፍ ልምዶች ጋር ለማጣጣም፣ የታክስ አለመግባባቶችን በፍትሐዊነት፣ በሰላማዊ መንገድና በቅልጥፍና ለመፍታት እንዲሁም የመንግሥትን የገቢ አሰባሰብ አቅም በታማኝነት ላይ መሥርቶ ለማጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ ያለው የሕግ ማዕቀፍ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ሐሳብና አስተያየት ከሰጡበት በኋላ ለዝርዝር ዕይታ ወደ ቋሚ ኮሚቴው መመራቱን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።
#hpr #agribusinesslaw #taxreform #agriculturaldevelopment #fiscalmodernization #ethiopianbroadcastingcorporation

3 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.