Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በዛሬው ዕለት በመላው ሀገሪቱ እየተካሄደ ባለው የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሒደት ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባወጡት ይፋዊ መልዕክት የኢትዮጵያን ሕዝብ "አስደናቂም ተአምረኛም" ሲሉ በከፍተኛ ደረጃ አድንቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መልዕክታቸው፣ ሕዝቡ በዘንድሮው ምርጫ የሀገር ወዳድነት እና የወል መሻቱን የመጠበቅ አቅሙን ዳግም ለዓለም ማሳየቱን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መራጩ ሕዝብ የገጠሙትን በርካታ የተፈጥሮ፣ የማኅበራዊ እና የጸጥታ ፈተናዎች ተቋቁሞ ድምፁን በመስጠቱ ከልብ የመነጨ ምስጋና አቅርበውለታል። በምስጋና መልዕክታቸው ላይም መራጩ ዜጋ ያሳለፋቸውን ውጣ ውረዶች በዝርዝር አስቀምጠዋል። በዚህም መሠረት ዜጎች የሌሊቱን ብርድና ጨለማ ሳይፈሩ፣ እንዲሁም የቀትሩ ፀሐይና ድንገተኛ ዝናብ ሳይበግራቸው በምርጫ ጣቢያዎች መገኘታቸውን አድንቀዋል።

ከዚህም ባሻገር መራጮች ሠርግ፣ ኀዘን፣ ወሊድና ሌሎች ማኅበራዊ ሁነቶችን ወደ ጎን በመተው በምርጫው መሳተፋቸውን፣ ረጃጅም ሰልፎች ሳያታክቷቸው፣ እንዲሁም የአካል ጉዳት፣ ሕመም እና እርጅና የሀገር ተስፋን ከማየት ሳይገድባቸው ድምፃቸውን መስጠታቸውን በከፍተኛ አክብሮት አውስተዋል። የነገ ሀገር ተረካቢ ጨቅላ ልጆቻቸውን አዝለው ድምፅ የሰጡ እናቶችን ትጋት ያወደሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከምንም በላይ ደግሞ የጠላት ጩኸትና ማስፈራሪያ ያላስቆማቸውን ዜጎች ጽናት የዴሞክራሲ እውነተኛ ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህ ሕዝብ በውጣ ውረዶች መካከል ያሳየው ጽናት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ለሀገር ሕልውና የተከፈለ ታላቅ መስዋዕትነት መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል። አያይዘውም በመጪው አምስት ዓመት ሥልጣን ለሚይዙ እና የሕዝብ ውክልና ለሚያገኙ አካላት ጥብቅ አደራ አስተላልፈዋል።

"ይሄንን ሕዝብ ማገልገል መታደል ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በምርጫው አሸንፈው ኃላፊነት ለሚቀበሉ ተመራጮች፣ ያከበራቸውን ሕዝብ አክብረው፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ይህንን ሁሉ ዋጋ የከፈለውን ዜጋ በንጽሕና እና በታማኝነት እንዲያገለግሉ ጥሪያቸውን በማቅረብ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.